በኡጋንዳ ፖሊስ ታስረው የነበሩ የአርሰናል እግር ኳስ ክለብ ደጋፊዎች ከእስር ተለቀቁ
የሀገሪቱ ፖሊስ ባሳለፍነው እሁድ 20 የክለቡ ደጋፊዎችን ማሰሩ ይታወሳል
ደጋፊዎቹን እስር የዳረጋቸው አርሰናል ዋንጫ መብላቱን የሚያሳይ ዋንጫ ይዛችኋል በሚል ነው
በኡጋንዳ ፖሊስ ታስረው የነበሩ የአርሰናል እግር ኳስ ክለብ ደጋፊዎች ከእስር ተለቀቁ።
ባለፈው እሁድ ጥር 14 ቀን 2015 ዓ.ም አርሰናልን ከማንችስተር ዩናይትድ ያገናኘው የእንግሊዝ ፕሪሚየር ሊግ ጨዋታ በአርሰናል የበላይነት መጠናቀቁ ይታወሳል።
አርሰናል ማንችስተር ዩናይትድን 3ለ2 በማሸነፍ መሪነቱን ያጠናከረበትን ይህን ጨዋታ በመመልከት ላይ የነበሩ ኡጋንዳዊያን የአርሰናል እግር ኳስ ክለብ ደጋፊዎች በወቅቱ በፖሊስ ታስረው ነበር።
እንደ ቢቢሲ ዘገባ በኡጋንዳ ጅንጃ ተብላ በምትጠራ ከተማ የሁለቱን ክለቦች ጨዋታ በማየት ላይ የነበሩ ሰዎች በፖሊስ ታስረዋል።
20 ደጋፊዎች አርሰናል ጎል ማስቆጠሩን ተከትሎ ድምጻቸውን ከፍ አድርገው ደስታቸውን ገልጸዋል በሚል ነበር በወቅቱ በፖሊስ ሊታሰሩ የቻሉት።
ላለፉት አራት ቀናት በእስር ላይ የነበሩ የአርሰናል ደጋፊዎች ዛሬ መለቀቃቸውን ቢቢሲ ዘግቧል።
እንደዘገባው ከሆነ ደጋፊዎቹ የታሰሩት በወቅቱ አርሰናል ዋንጫ መብላቱን የሚያሳይ ተመሳሳይ አርቲፊሻል ዋንጫ ይዛችሁ ጨፍራችኋል በሚል ነው።
ፖሊስ ደጋፊዎቹ ዋንጫ መሰል ነገር ይዘው መጨፈራቸው የማንችስተር ክለብ ደጋፊዎችን በማስቆጣት ወደ ግጭት እንዲገቡ ያነሳሳል በሚል እንዳሰራቸው ተገልጿል።
አርሰናል ተቀናቃኙ ማንችስተር ዩናይትድን ማሸነፉን ተከትሎ የፕሪሚየር ሊጉን በ50 ነጥብ መሪነቱን አጠናክሯል።
የማሸነፊያ ጎሎቹን ኤዲ ኔኪታህ ሁለት ጎል እንዲሁም ቡካዮ ሳካ አንድ ጎል ለአርሰናል አስቆጥረዋል።
ማንችስተርን ከሽንፈት ያልታደጉ ሁለት ጎሎች ማርከስ ራሽፎርድ እና ተከላካዩ ማርቲኔዝ አስቆጥረዋል።