ጋሪ ኔቪል “አርሰናል በ8 ነጥብ ቢመራም ፕሪሚየር ሊጉን አያሸንፍም” አለ
የቀድሞው የዩናይትድ ተጫዋች አርሰናሎች ሁለት ከባድ ጨዋታዎች እንደሚጠብቋቸው መዘንጋት የለባቸውም ብሏል
ጋሪ ኔቪል፤ በውድድር ዘመኑ “ ሲቲዎች ዋንጫ ያነሳሉ” ሲል በልበ ሙሉነት ተናግሯል
በሰሜን ለንደን ደርቢ በቶተንሃም ሆትስፐር ስታዲየም አርሰናል ቶተንሃምን 2-0 በማሸነፍ የፕሪሚየር ሊጉ የደረጃ ሰንጠረዥ አናት ላይ ተቀምጧል።
ውጤቱም አርሰናል ሻምፒዮኑን ማንቸስተር ሲቲን በስምንት ነጥብ እንዲበልጥ አድርጎታል።
ኒውካስል እና ማንቸስተር ዩናይትድ ደግሞ በ38 ነጥብ በግብ ክፍያ ተበላልጠው ሶስተኛ እና አራተኛ ደረጃን ይዘዋል።
በዚህም በርካታ የእግር ኳስ አፍቃሪዎች እና ተንታኞች በስፔናዊው አሰልጣኝ ማይክል አርቴታ የሚሰለጥኑት መድፈኞቹ ከበርካታ አመታት በኋላ የሊጉን ዋንጫ በማንሳት ታሪክ ሊሰሩ ይችላሉ የሚል ግምት ማሳደራቸው አልቀረም፡፡
በርካቶች ይህን ኃሳብ ቢያንጸባርቁም የቀድሞ የማንቸስተር ዩናይትድ ተጨዋችና አምበል ጋሪ ኔቪል “አርሰናል በዘንድሮው የውድድር ዘመን ፕሪሚየር ሊጉን በ8 ነጥብ ቢመራም አያሸንፍም” ብሏል፡፡
የሊጉን ዋንጫ ማን ያነሳ ይሆን..? በሚል አስተያየቱን እንዲሰጥ የተጠየቀው ጋሪ ኔቪል ፤ በውድድር ዘመኑ “ ሲቲዎች ዋንጫ ያነሳሉ እንዲሁም ዩናይትዶች የውድድር ዘመኑን ከነሱ (መድፈኞቹ) በላይ ሆነው ያጠናቅቃሉ ብየ አምናለሁ” ሲል በእርግጠኝነት ተናግሯል፡፡
"እኔ ከማን ሲቲ ይልቅ አርሰናል ሊጉን ቢያሸንፍ እመርጣለሁ ምክንያቱም ለፕሪምየር ሊጉ ፍጹም ስሜት የሚፈጥር ይመስለኛል የሚለው ኔቪል ፤ ይሁን እንጅ ማንቸስተር ሲቲዎች የሆነ ወቅት ላይ መብለጣቸው አይቀርም ብሏል፡፡
አርሰናል ከሲቲ ጋር ሁለት ከባድ ጨዋታዎች እንደሚጠብቋቸው ያስታወሰው ኔቪል፤ ኤርሊንግ ሀላንድ ከጉዳት ሲመለስ ነገሮች ምን ያህል ለመድፈኞች ከባድ እንደሚሆኑ መገመት እንደሚቻልም ተናግሯል፡፡
“ኤርሊንግ ሃላንድ ወደ ሜዳ ተመልሶ ቡድኑ ወደ ማጥቃት ከገባና ተከላካይ ክፍሉን ካስተካከለ ፣ሲቲ ያሸንፋል ብዬ አስባለሁ” ሲልም አክሏል ጋሪ ኔቪል፡፡
አርሰናል ባለበት ሁኔታ ሊቀጥል እንደሚችል መገመት ይቻላል ወይ? ተብሎ በስካይ ስፖርት የተጠየቀው ኔቪል “አይመስለኝም!” የሚል ምላሽ ሰጥቷል፡፡
"የአርሰናል ደጋፊዎች ላለፉት አራት ወራት ሲያደርጉት እንደነበረው ሁሉ እንደሚደበድቡኝ አውቃለሁ፣ ቢያሸንፉም ደስ ይለኛል፤ ነገር ግን እኔ እንዳመስበው ወጣት አሰልጣኙ ማይክል አርቴታ፣ የአንቶኒዮ ኮንቴ፣ የርገን ክሎፕ ፣ ፔፕ ጋርዲዮላ እና ጆዜ ሞሪንሆ ስኬት ላይ መድረስ አይችልም” ሲልም አብራርቷል ኔቪል፡፡
አክሎም አርቴታ በሊጉ የስኬታማ አሰልጣኞች ተርታ ለመሰለፍ አሁንም የሊጉን ዋንጫ ማሸነፍ ይጠበቅበታል ብሏል የቀድሞ የማንቸስተር ዩናይትድ ተጨዋቹ ጋሪ ኔቪል፡፡