ሊቋቋም በነበረው ሱፐር ሊግ ምክንያት ዩናይትድ እና አርሰናልን ጨምሮ 9 ታላላቅ የአውሮፓ እግር ኳስ ቡድኖች ተቀጡ
ማህበሩ ለሚያዘጋጃቸው ውድድሮች ያላቸውን ቁርጠኝነት የሚያሳውቅ መግለጫ አቅርበዋልም
ቡድኖቹ የተቀጡት በአውሮፓ እግር ኳስ ማህበር ሲሆን ድርጊቱ ጥፋት መሆኑን አምነው ይቅርታ ጠይቀዋል
ሱፐር ሊግን ሊያቋቁሙ ሲንቀሳቀሱ ከነበሩ 12 ታላላቅ የእግር ኳስ ክለቦች መካከል በ9ኙ ላይ የገንዘብ ቅጣትን ጨምሮ ሌሎች ቅጣቶችን መጣሉን የአውሮፓ እግር ኳስ ማህበር አስታወቀ፡፡
ማህበሩ 9ኙ ክለቦች እንቅስቃሴው ጥፋት መሆኑን አምነው ይቅርታ መጠየቃቸውን አስታውቋል፡፡
ክለቦቹ ጉዳዩን ለማስታረቅ ሲባል ማህበሩ ለሚያዘጋጃቸው ውድድሮች ያላቸውን ቁርጠኝነት የሚያሳውቅ መግለጫ ያቀረቡም ሲሆን በአህጉራዊ ውድድሮች ከሚያገኙት ዓመታዊ ገቢ 5 በመቶ ያህሉን ለመቀነስ ተስማምተዋል፡፡ ይህንንም በፊርማቸው አረጋግጠዋል፡፡
ሆኖም ባርሴሎና፣ሪያል ማድሪድ እና ጁቬንተስ እስካሁን መግለጫውን ፈርመው መቀበላቸውን አላሳወቁም፡፡
ይህን ተከትሎ ማህበሩ አሁንም ከድርጊታቸው ለመቆጠብ ባልፈቀዱ ክለቦች ላይ እርምጃ ለመውሰድ የሚያስችል ሙሉ ስልጣን እንዳለው አስታውቋል፡፡
ጉዳዩን የዲሲፕሊን ጉዳዮችን ወደሚመለከተው የማህበሩ አካል በቶሎ እንደሚመራውም ነው ያስታወቀው፡፡
ከማህበሩ ጋር የተስማሙት 9ኙ ክለቦች ቶተንሃም፣አርሰናል፣ ማንችስተር ሲቲ፣ ማንችስተር ዩናይትድ፣ ቼልሲ፣ ሊቨርፑል፣አትሌቲኮ ማድሪድ፣ ኢንተር ሚላን እና ኤሲ ሚላን ናቸው፡፡
የማህበሩ ፕሬዝዳንት አሌክሳንደር ሴፈሪን ክለቦቹ ጥፋታቸውን አምነው ወደፊት ለአውሮፓ እግር ኳስ ያላቸውን አበርክቶ እና ቁርጠኝነት በቶሎ አሳይተዋል፡፡
ይህን ካለደረጉ ቀሪ ክለቦች ጋር መነጋገራችን ይቀጥላልም ብለዋል ፕሬዝዳንቱ፡፡
ከዓመታዊ ገቢያቸውን 5 በመቶ ያህል ለመቀነስ የተስማሙት ክለቦቹ ለታዳጊዎች እግር ኳስ ልማት የሚውል የ15 ሚሊዬን ዩሮ ድጋፍ ለማድረግም ተስማምተዋል፡፡
ክለቦቹ ማህበሩ በሚያዘጋጃቸው የየደረጃው ውድድሮች ብቻ መሳተፋቸውን እንደሚቀጥሉ የገለጹም ሲሆን ከዚያ ውጭ በሌሎች ባልተፈቀዱ ውድድሮች ለመሳተፍ ከፈለጉ መቶ ሚሊዬን ዩሮ ለመክፈልም ጭምር ነው የተስማሙት፡፡