የአርሰናል እና ማንቸስተር ሲቲ ፍልሚያ የሊቨርፑልን ሻምፒዮንነት ይወስናል?
መድፈኞቹ ከየካቲት 2023 ወዲህ በኤምሬትስ በፔፕ ጋርዲዮላ ቡድን አልተሸነፉም
የሰሜን ለንደኑ ክለብ ከሲቲ ጋር ከተገናኘባቸው 55 የፕሪሚየር ሊግ ጨዋታዎች በ24ቱ አሸንፏል
የእንግሊዝ ፕሪሚየር ሊግ 24ኛ ሳምንት ዛሬም ቀጥሎ ሲካሄድ አርሰናል በኤምሬትስ ማንቸስተር ሲቲን የሚያስተናግድበት ጨዋታ ይጠበቃል።
ምሽት 1 ስአት ከ30 የሚደረገው ጨዋታ የፕሪሚየር ሊጉን ሻምፒዮን የመወሰን አቅሙ ከፍ ያለ ነው።
በ47 ነጥብ ሁለተኛ ደረጃ የተቀመጡት መድፈኞቹ በፔፕ ጋርዲዮላ ቡድን ከተሸነፉ ከሊቨርፑል ጋር ያላቸው የነጥብ ልዩነት ባለበት ዘጠኝ ነጥብ ይቀጥላል፤ ቀያዮቹ ቀሪ አንድ ጨዋታቸውን ካሸነፉ ደግሞ ልዩነቱ ወደ 12 ከፍ ይላል።
የሰሜን ለንደኑ ክለቡ ከ2017 እስከ 2023 ድረስ በማንቸስተር ሲቲ በተከታታይ 12 ጊዜ ተሸንፏል።
ለመጨረሻ ጊዜ በየካቲት 2023 በኤምሬትስ ከተሸነፉ ወዲህ ግን በሜዳቸው ሽንፈት አላስተናገዱም። ባለፉት ሶስት ተከታታይ የፕሪሚየር ሊግ ግንኙነታቸውም በአንዱ አሸንፈው በሁለቱ ነጥብ ተጋርተዋል።
አርሰናል እና ማንቸስተር ሲቲ ከተገናኙባቸው 55 የፕሪሚየር ሊግ ጨዋታዎች መድፈኞቹ በ24ቱ አሸንፈው በ12ቱ አቻ ተለያይተዋል።
ባለፉት አመታት በፕሪሚየር ሊጉ ወርቃማ ድል ያስመዘገበው ማንቸስተር ሲቲ በዘንድሮው የውድድር አመት በውጤት ቀውስ ውስጥ ገብቶ ከአርሰናል በስድስት ነጥብ ዝቅ ብሎ አራተኛ ደረጃ ላይ ይገኛል።
የፔፕ ጋርዲዮላ ቡድን በፕሪሚየር ሊጉ እስከ 13ኛ ደረጃ ካሉ ክለቦች ከሜዳው ውጭ ያሸነፈው አንድ ቡድንን ብቻ ነው።
በሁሉም ውድድሮች ከሜዳ ውጭ ጨዋታቸው ካደረጓቸው ካላፉት 12 ጨዋታዎች በስምንቱ ነጥብ መጣላቸውንም የስካይ ኒውስ ዘገባ ያሳያል።
ባለፉት ሁለት አመታት ለሻምፒዮንነት ብርቱ ፉክክር ሲያደርጉ የቆዩት አርሰናል እና ማንቸስተር ሲቲ ዘንድሮ ለአርኔ ስሎቱ ሊቨርፑል እጅ የሰጡ መስለዋል።
በውድድሩ አመት መጀመሪያ በኢትሃድ ያሳዩት ብርቱ ፉክክር በዛሬ ምሽቱ ጨዋታ ይደገማል ወይ የሚለውም አጠራጣሪ ነው።
መድፈኞቹ ከመስከረሙ ትንቅንቅ ከ133 ቀናት በኋላ በኤምሬትስ ማንቸስተር ሲቲን በማሸነፍ ወደ ዋንጫ ፉክክሩ ለመመለስ እንደሚተጉ አሰልጣኛቸው ሚኬል አሬታ ተናግሯል።
ካለፉት አምስት ጨዋታዎች 13 ነጥብ መሰብሰብ የቻሉት ፔፕ ጋርዲዮላም ከሊቨርፑል ለመድረስ አቀበት ቢመስልም የምሽቱን ጨዋታ ማሸነፍ እንደሚገባ ተጫዋቾቻቸውን አሳስበዋል።
በስድስት ጨዋታዎች ስድስት ጎሎች ካስቆጠረው ሃላንድ በኤምሬትስ ግብ ይፈልጋሉ።
ኖርዌያዊው አጥቂ ክለቡ ከአርሰናል ጋር ባደረጋቸው ሰባት ጨዋታዎች ተሰልፎ ሶስት ጎሎችን ያስቆጠረ ሲሆን፥ የመድፈኞቹ ጠንካራ የተከላካይ መስመር ባለፉት አራት ጨዋታዎች ፈታኝ ሆነውበታል።
ከምሽቱ የኤምሬትስ ተጠባቂ ጨዋታ አስቀድሞ ማንቸስተር ዩናይትድ ከክሪስታል ፓላስ ፤ ብሬንትፈርድ ከቶተንሀም 11 ስአት ላይ ይጫወታሉ።