ትውልደ ኢትዮጲያዊቷ ናኦሚ ግርማ ክብረወሰን በሰበረ ዋጋ ቼልሲን ተቀላቀለች
የአሜሪካ የሴቶች ብሔራዊ ቡድን ተከላካይ መስመር ተጫዋቿ ናዮሚ በሳንዲያጎ ዌቭ ክለብ ስትጫወት ቆይታለች
የ24 አመቷ ወጣት ከሰማያዊዎቹ ጋር ለ4 አመት ተኩል የሚያቆያትን ውል በ1.1 ሚሊየን ዶላር ፈርማለች
ትውልደ ኢትዮጵያዊቷ የአሜሪካ የሴቶች ብሔራዊ ቡድን ተከላካይ ናኦሚ ግርማ በሴቶች እግር ኳስ ታሪክ የመጀመርያ የሚሊየን ዶላር ተጫዋች ሆና ቼልሲን ተቀላቅላለች፡፡
የ24 አመቷ ወጣት ካሳንዲያጎ ዌቭ በ 900 ሺህ ፓውንድ (1.1 ሚሊዮን ዶላር) የአራት አመት ተኩል ኮንትራት ለሰማያዊዎቹ ፈርማለች፡፡
ከዚህ ቀደም በሴት እግር ኳስ ተጫዋች ዝውውር ክብረ ወሰኑን ይዛ የነበረችው ዛምቢያዊቷ አጥቂ ራቼል ኩንዳናንጂ ነበረች፡፡
ተጫዋቿ ባሳለፍነው አመት በ788 ሺህ ዶላር ከማድሪድ ወደ ቤይ እግር ኳስ ቡድን ስትቀላቀል የክብረ ወሰኑ ባለቤት ሆና ነበር፡፡
ናኦሚ ግርማን ጨምሮ ቼልሲ ተጫዋቾችን በማስፈረም ሪከርዱን ሲሰብር ይህ ለሶስተኛ ጊዜ ሲሆን፤ ፔርኒል ሃርደርን በ2020 በ355 ሺህ ዶላር እና በ2024 ሜይራ ራሚሬዝን በ542 ዶላር አስፈርሟል።
ለአሜሪካ ብሔራዊ ቡድን 44 ጨዋታዎች ላይ የተሰለፈችው ናኦሚ በፓሪስ ኦሎምፒክ ከብሔራዊ ቡድኑ ጋር የወርቅ ሜዳሊያን ማሳካት ችላለች፡፡
በተጨማሪም በ2023 በአውስትራሊያ እና በኒውዚላንድ በተካሄደው የሴቶች አለም ዋንጫ በነበራት ሚና የአሜሪካ የአመቱ ምርጥ ሴት እግር ኳስ ተጫዋች ሆና ተመርጣለች፡፡
ለሳንዲያጎ ዌቭ ክለብ በሶስት የውድድር ዘመኖች 72 ጨዋታዎች ላይ ተሰልፋ መጫወት የቻለች ሲሆን በ2023 በፊፋ የምርጥ የእግር ኳስ ተጫዋቾች ሽልማት ውስጥ ዕጩ በመሆን ቀርባ ነበር፡፡
ወጣቷ ተጫዋች ከፊርማው በኋላ ባደረገችው ንግግር ቼልሲ የአሸናፊነት አስተሳሰብ ያለው ቡድን ነው። ከዚህ ባለፈም ለመማር እና ለማደግ ምቹ ከባቢ ያለው በመሆኑ ቡድኑን በመቀላቀሌ ደስተኛ ነኝ ብላለች፡፡
ከቼልሲ ጋር 12 አመታትን ያሳለፈችው እና ሰባት የሱፐር ሊግ ዋንጫዎችን ያነሳቸው የአሜሪካ የሴቶች ብሔራዊ ቡድን አሰልጣኝ ኤማ ሄይስ በእድሜ ዘመኔ ካየኋቸው ምርጥ ተከላካዮች መካከል ናኦሚ አንዷ ናት ስትል ምስክርነቷን ሰጥታለች፡፡
በትላንትናው ዕለት ከደጋፊዎች ጋር በስታምፎርድ ብሪጅ የተዋወቀችው ናኦሚ በሰማያዊዎቹ ቤት ለሚቀጥሉት አራት አመት ተኩል 16 ቁጥር ማሊያን ለብሳ የምትጫወት ይሆናል፡፡
ቼልሲ በአሁኑ ወቅት በሴቶች ሱፐር ሊግ ከማንችስተር ዩናይትድ በ7 ነጥብ ርቆ አንደኛ ደረጃ ላይ ይገኛል፡፡