የአምናው ሻምፒዮን ማንቸስተር ሲቲ እና አርሰናል ከሻምፒዮንስ ሊግ ተሰናበቱ
የእንግሊዝ ክለቦች በተመሳሳይ ቀን በሻምፒዮንስ ሊግ የሩብ ፍጻሜ ጨዋታዎች ተሸንፈው ሲሰናበቱም የመጀመሪያው ሆኗል
ሪያል ማድሪድ እና ባየርሙኒክ በግማሽ ፍጻሜው ይፋለማሉ
የአውሮፓ ሻምፒዮንስ ሊግ የሩብ ፍጻሜ የመልስ ጨዋታዎች ትናንት ምሽት ሲደረጉ አርሰናልና ማንቸስተር ሲቲ ከውድድሩ ውጭ ሆነዋል።
በአሊያንዝ አሬና ከጀርመኑ ባየር ሙኒክ ጋር የተጫወተው አርሰናል 1 ለ 0 ተሸንፏል፤ በድምር ውጤትም 3 ለ 2 በሆነ ውጤት ግማሽ ፍጻሜ የመድረስ ጥረቱ ሳይሳካ ቀርቷል።
ለቶማስ ቱኸል ቡድን በ63ኛው ደቂቃ በጆሽዋ ኪሚች ጎል አሸንፎ በቡንደስሊጋው በባየር ሊቨርኩሰን የተነጠቀውን ድል በሻምፒዮንስ ሊጉ ለማካካስ እድል አግኝቷል።
የአምናው ሻምፒዮን ማንቸስተር ሲቲ በበኩሉ በኢትሃድ ሪያል ማድሪድን አስተናግዶ በመለያ ምት ተሸንፎ ለሁለት ተከታታይ አመታት ሶስትዮሽ ዋንጫ የማሳካት ግስጋሴው ተጨናግፎበታል።
ብራዚላዊው ሮድሪጎ ሪያል ማድሪድን ቀዳሚ ያደረገች ጎል በ12ኛው ደቂቃ ሲያስቆጥር ኬቭን ደ ብሩይነ በ63ኛ ደቂቃ አቻ አድርጓል።
ተጨማሪው ስአት በድምር ውጤት 4 ለ 4 በመጠናቀቁ ወደ መለያ ምት አምርተው የካርሎ አንቸሎቴ ቡድን ማሸነፍ ችሏል። በርናንዶ ሲልቫ እና ማቲዮ ኮቫቺች መለያ ምት የሳቱ የሲቲ ተጫዋቾች ናቸው።
በአውሮፓ ሻምፒዮንስ ሊግ ታሪክ በጥሎ ማለፍ ጨዋታዎች ሁለት የእንግሊዝ ክለቦች በተመሳሳይ ቀን የተሰናበቱበት ምሽት ባየር ሙኒክና ሪያል ማድሪድን የግማሽ ፍጻሜ ተፋላሚ አድርጓል።
ከጨዋታው በኋላ አስተያየታቸውን የሰጡት የመድፈኞቹ አሰልጣኝ ሚኬል አርቴታ በኤምሬትስ ሁለት ጎሎችን ማስተናገዳቸው እንዳስቆጫቸው ጠቅሰው ከሰባት አመት በኋላ ወደ ሻምፒዮንስ ሊጉ ናቸው ወደ ለፍጻሜ ለመድረስ ከፍተኛ ፍላጎት እንደነበረው ተናግረዋል።
በፕሪሚየር ሊጉ በሲቲ በሁለት ነጥብ ተበልጦ ሁለተኛ ደረጃ የተቀመጠው አርሰናል ፥ ቀሪ ጨዋታዎችን አሸንፎ ዋንጫውን ለማንሳት ይታገላል ነው ያሉት።
የማንቸስተር ሲቲው አሰልጣኝ ፔፕ ጋርዲዮላ በበኩላቸው በኢትሃድ ቡድናቸው ጨዋታውን መቆጣጠር ቢችልም የተገኙ እድሎችን ወደ ጎል አለመቀየሩ ዋጋ አስከፍሎናል ብለዋል።
ቀጣይ ትኩረታቸውንም ፕሪሚየር ሊግ እና ኤፍኤ ካፕ ላይ እንደሚያደርጉም ነው የተናገሩት።