ምባፔ የሻምፒዮንስ ሊግ ዋንጫ በማንሳት ከፒኤስጂ ጋር ይለያይ ይሆን?
ፈረንሳዊው አጥቂ ፒኤስጂ የ5 ጊዜ የሻምፒዮንስ ሊግ አሸናፊውን ባርሴሎና በረታበት ግጥሚያ ሁለት ጎሎችን አስቆጥሯል
ፒኤስጂ አትሌቲኮ ማድሪድን ካሸነፈው ዶርትሙንድ ጋር በሻምፒዮንስ ሊጉ ግማሽ ፍጻሜ ይገናኛል
ኪሊያን ምባፔ ኮከብ ተጫዋቾች ለክለባቸው በወሳኝ ወቅት ማድረግ የሚገባቸውን አድርጓል።
የ25 አመቱ አጥቂ ፒኤስጂ በሻምፒዮንስ ሊጉ የሩብ ፍጻሜ የመልስ ጨዋታ ባርሴሎናን ሲገጥም ሁለት ወሳኝ ጎሎችን አስቆጥሮ ክለቡን ለግማሽ ፍጻሜ አድርሷል።
በፓርክ ደ ፕሪንስ 3 ለ 2 ተሸንፎ የነበረው ፒኤስጂ በመልሱ ጨዋታ የአምስት ጊዜ የሻምፒዮንስ ሊግ አሸናፊውን ባርሴሎና 4 ለ 1 አሸንፎ በድምር ውጤት 6 ለ 4 ወደ ግማሽ ፍጻሜ ደርሷል።
በ61ኛ ደቂቃ በፍጹም ቅጣት ምት፤ በ89ኛው ደቂቃ ደግሞ ለራሱ ሁለተኛዋን ለክለቡ ደግሞ አራተኛዋን ጎል ያስቆጠረው ምባፔ፥ “ከፒኤስጂ ጋር ሻምፒዮንስ ሊግ ማንሳት የሁልጊዜም ምኞቴ ነው” ብሏል።
ምባፔ የተወለደባት ከተማ ፓሪስ ክለብን ለዌንብሌዩ የፍጻሜ ፍልሚያ ለማድረስ አንድ ጨዋታ ብቻ ይቀረዋል፤ አትሌቲኮ ማድሪድን አሸንፎ ለግማሽ ፍጻሜ ከደረሰው ቦርሺያ ዶርትሙንድ ጋር።
በዚህ የውድድር አመት በ10 የሻምፒዮንስ ሊግ ጨዋታዎች ስምንት ጎሎችን ያስቆጠረው ፈረንሳዊው አጥቂ በሻምፒዮንስ ሊግ የጥሎ ማለፍ ጨዋታዎች ከሜዳ ውጭ በርካታ ጎሎችን በማስቆጠር ክርስቲያኖ ሮናልዶን ይከተላል።
ሮናልዶ በ23 ጨዋታዎች 39 ጎሎችን ከመረብ ሲያገናኝ ምባፔ በ15 ጨዋታዎች 12 ጎሎችን ማስቆጠር ችሏል።
ፒኤስጂ እና ምባፔ በውድድሩ አመት መጠናቀቂያ ላይ ይለያያሉ መባሉን ተከትሎ ፈረንሳዊው አጥቂ የአውሮፓን ትልቁን ዋንጫ ከፓሪሱ ክለብ ጋር እንዲያነሳ በርካቶች ይመኙለታል።
ምባፔ ባለፈው የካቲት ወር ከሪያል ማድሪድ ጋር የአምስት አመት ኮንትራት ለመፈረም መዘጋጀቱን ለፒኤስጂ ፕሬዝዳንት ናስር አል ካሊፊ መናገሩ ይታወሳል።
ተጫዋቹ ወደ ስፔኑ ክለብ እንደሚዛወር ቢገልጽም ለክለቡ በ42 ጨዋታዎች 41 ጎሎችን ማስቆጠሩን ነው ቢቢሲ የዘገበው።
የፒኤስጂ ባለቤት የኳታር ስፖርትስ ኢንቨስትመንት ከምባፔ ጋር ሲለያይ የአውሮፓ ሻምፒዮንስ ሊግ ዋንጫን በማንሳት እንዲሆን ይጠብቃል።
ቡድኑ ከ2011 ወዲህ ዘጠኝ የሊግ 1 ዋንጫዎችን ማንሳት ቢችልም በሻምፒዮንስ ሊጉ ሻምፒዮን ሆኖ ማየት ዋነኛ ግባቸው እንደሆነ ባለቤቶቹ ሲናገሩ ይሰማል።
ፒኤስጂ በ2020 ለፍጻሜ ደርሶ በባየር ሙኒክ 1 ለ 0 ተሸንፎ ዋንጫውን ማጣቱ አይዘነጋም። ከዚህ የፍጻሜ ጨዋታ በኋላ ባሉ የሻምፒዮንስ ሊግ ውድድሮች ላይ በጥሎ ማለፍ ጨዋታዎች መሰናበቱ ፒኤስጂ በአውሮፓ ተፎካካሪ ቡድን ነው ወይ የሚለውን ጥርጣሬ አስከትሎ ነበር።
ኪሊያን ምባፔ ይህን ተረት ለማድረግ ሁለት ጨዋታዎችን በድል ማጠናቀቅ ይቀረዋል።