በዲ.አር.ኮንጎ አንድ ሬስቶራንት ውስጥ አጥፍቶ ጠፊ ባደረሰው የቦምብ ጥቃት ቢያንስ 5 ሰዎች ሞቱ
ፕሬዝዳንት ፌሊክስ ቲሺሴኬዲ ድሪጊቱን "አስጸያፊ" ሲሉ በትዊትር ገጻቸው ባጋሩት ጽሁፍ አውግዘዋል
ጥቃት ያደረሰው “ኤ.ዲ.ኤፍ” እንደሆነ ቢነገርም እስካሁን ኃላፊነቱን የወሰደ አካል የለም
በዲሞክራቲክ ኮንጎ ምስራቃዊ ከተማ ቤኒ በአንድ ሬስቶራንት በፈነዳ የአጥፍቶ ጠፊ ቦምብ ቢያንስ አምስት ሰዎች መሞታቸውን የቤኒ ባለስልጣናት አስታወቁ።
ፍንዳታው የተፈፀመው ሰዎች “ኢንቦክስ ባር” በተባለ ሬስቶራንት የገና በዓልን በማክበር ላይ ሳሉ እንደሆነም ነው የቤኒ የጸጥታ ባለስልጣን የተናገሩት።
- የፀጥታው ምክር ቤት በዲሞክራቲክ ሪፐብሊክ ኮንጎ የሚገኘውን “የተመድ የሰላም ማስከበር ተልዕኮ” አራዘመ
- ኡጋንዳ እና ዲ.አር ኮንጎ በኤ.ዲ.ኤፍ አማጺ ቡድን ላይ “ስኬታማ”ጥቃት መሰንዘራቸውን አስታወቁ
ጥቃቱን ተከትሎ መግለጫ የሰጡት የክልሉ ርዕሰ መስተዳድር ቃል አቀባይ ጄኔራል ኢኬንጌ ሲልቫን “ፖሊስ ቦምቡን ይዞ የነበረው ግለሰብ ወደ ህንጻው እንዳይገባ ከልክሎት የነበረ ቢሆንም ግለሰቡ መግቢያ በሩ ላይ ቦምቡን ራሱ ላይ በማፈንዳቱ ራሱንና እና ሌሎች አምስት ሰዎችን ገድሏል እንዲሁም ሌሎች 14 ሰዎች ደግሞ ጉዳት ደርሶባቸዋል” ብሏል፡፡
ጥቃት ያደረሰው የጥምር ዲሞክራሲያዊ ኃይሎች [Allied Democratic Forces] የተባለውና ከአይ.ኤስ ጋር ግንኙነት እንዳለው የሚነገረው ታጣቂ ቡድን እንደሆነ እንደሆነም ቃል አቀባዩ ሲልቫን ተናግሯል፡፡
እንደ ሮይተረስ ዘገባ ከሆነ ግን፤ እስካሁን ድረስ ለደረሰው ጥቃት ኃላፊነቱን የወሰደ አካል የለም።
የዲሞክራቲክ ሪፐብሊክ ኮንጎ ፕሬዝዳንት ፌሊክስ፡ ቲሺሴኬዲ ድሪጊቱን "አስጸያፊ" እና መንግሰታቸው በጽኑ የሚያወግዘው እንደሆነ በትዊትር ገጻቸው ባሰፈሩት ጽሁፍ አጋርቷል፡፡
ጥቃቱ ሲፈፀም ከ30 በላይ የሚሆኑ ሰዎች በአንድ ሬስቶራንት ውስጥ ተሰባስበው የገና በዓልን እያከበሩ እንደነበር ሁለት የዐይን ምስክሮች ነግረውኛል ያለው ደግሞ የፈረንሳዩ የዜና ወኪል /ኤ.ኤፍ.ፒ/ ነው፡፡
በወቅቱም በሬስቶራንቱ ህጻናትና የግዘቱ ባለስልጠናት እንደነበሩም ተነግሯል።
" እዚያ ተቀምጬ ነበር፤ በስፍራው ሞተር ሳይክል ቆሞ ነበር፤ድንገት ሞተር ሳይክሉ ተነ፤ ከዚያም ከፍተኛ ድምጽ ተሰማ " ሲል ኒኮላስ ኢኪላ የተባለ የራዲዮ ፕሮግራም አቅራቢ ለኤኤፍፒ ምስክርነቱን ሰጥቷል።
ፍንዳታው ከተከሰተ በኋላም በአገሪቷ ምሽራቃዊ ክፍል ለተጣለው አስቸኳይ ጊዜ ኃላፊነት ያላቸው የጦር ባለሥልጣናት ነዋሪዎች ለደህንነታቸው ሲሉ ወደ ቤታቸው እንዲሄዱ አሳስበዋቸዋል።
ከቅርብ ሳምንታት ወዲህ በቤኒ በጦሩ እና በእስላማዊ ታጣቂዎቹ መካከል ተደጋጋሚ ግጭት ሲከሰት ይስተዋላል።
ህዳር ወር ላይ የኮንጎ እና የኡጋንዳ ኃይሎች በተደጋጋሚ የሚፈፀሙ ጥቃቶች ለማስቆም በእስላማዊ ታጣቂ ቡድኑ ኤ.ዲ.ኤፍ ላይ በጋራ እርምጃ መውሰድ መጀመራቸው የሚታወቅ ነው።
የኡጋንዳ ባለስልጣናት ቡድኑ በዋና መዲናዋ ካምፓላ ጨምሮ በሀገሪቷ በተደጋጋሚ ለተፈፀሙ ጥቃቶች ኤ.ዲ.ኤፍ ተጠያቂ እንደሆነ ሲገልጹ ቆይቷል።
እንደፈረንጆቹ በ1990ዎቹ መንግሥት በሙስሊሞች ላይ በሚወስደው እርምጃ ቅር በተሰኙ ኡጋንዳውያን እንደተቋቋመ የሚነገርለት ታጣቂ ቡዱኑ፤ አሁን ላይ ይንቀሳቀሱበት ከነበረው ከምዕራብ ኡጋንዳ ተወግዶ ድንበር በመሻገር ወደ ዲሞክራቲክ ኮንጎ እንደገባ ይነገራል፡፡
ከዚያም በምስራቅ ዲሞክራቲክ ኮንጎ ውስጥ እራሱን በይበልጥ በማደራጀት ባለፉት አስርት ዓመታት ውስጥ በክርስቲያኖች ላይ የሚደርሰውን ጥቃት ጨምሮ በሺዎች ለሚቆጠሩ ሰዎች ግድያ ተጠያቂ ሆኗል።
መጋቢት ወር ላይ አሜሪካ ኤዲኤፍን ከአይኤስ ጋር ግንኙነት ባላቸው የሽብር ቡድኖች ዝርዝር ውስጥ ማስገባቷ የሚታወስ ነው።