በዲ አር ኮንጎ የተከሰተው አዲስ ገዳይ በሽታ ምንድን ነው?
የሀገሪቱ የጤና ባለስልጣናት በበሽታው 143 ሰዎች ህይወት ማለፉን አረጋግጠዋል
ራስ ምታት ፣ ሳል ፣ የደም ማነስ እና ከፍተኛ ትኩሳት የበሽታው ምልክቶች እንደሆኑ ተገልጿል
በዴሞክራቲክ ሪፐብሊክ ኮንጎ (ዲአርኮንጎ) ምንነቱ ባልታወቀ በሽታ 143 ሰዎች መሞታቸው ተነግሯል።
በደቡብ ምዕራብ ኮንጎ የተከሰተው ጉንፋን መሰል በሽታ ላለፉት ሁለት ሳምንታት የበርካታ ሰዎችን ህይወት መቅጠፉን ተከትሎ የሀገሪቱ የጤና ባለስልጣናት ተጨማሪ ምርምሮችን እያደረጉ ነው፡፡
የሟቾች ቁጥር የተመዘገበው ከፈረንጆቹ ህዳር 10 እስከ ህዳር 25 ባለው ጊዜ ውስጥ ፓንዚ በተባለው የሀገሪቱ ግዛት ሲሆን ምልክቶቹ ትኩሳት፣ ራስ ምታት፣ ሳል እና የደም ማነስን እንደሚያካከትት ተገልጿል፡፡
የግዛቱ ምክትል አስተዳዳሪ እስካሁን ቁጥራቸው ከ67 እስከ 143 የሚጠጉ ሰዎች በሽታው መሞታቸውን አረጋግጠው ስርጭቱን ለመቆጣጠር ምልክቱን የሚያሳዩ ሰዎችን ለይቶ ማቆያ ውስጥ እየገቡ ይገኛሉ ብለዋል፡፡
የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች በበኩላቸው በገጠሩ የፓንዚ ግዛት በበሽታው የተያዙ ሰዎች ቁጥር እየጨመረ በመምጣቱ የጤና ተቋማት ለከፋ የመድሃኒት እጥረት መጋለጣቸውን ገልጸው ከጉዳዩ አሳሳቢነት አንጻር መንግስት የሰጠው ትኩረት ዝቅተኛ ነው ሲሉ ተችተዋል፡፡
በአሁኑ ሰአት የጤና ባለሙያዎች ናሙናዎችን በመወሰድ የበሽታውን ምንነት ለማወቅ ምርምር እያደረጉ እንደሚገኙ የተናገሩት የጤና ባለስልጣናቱ አለም አቀፍ አጋሮች የላብራቶሪ እና የህክምና ቁሳቁሶች ድጋፍ እንዲያደርጉ ጠይቀዋል፡፡
በተጨማሪም ህብረተሰቡ ስርጭቱ እንዳይባባስ ጥንቃቄ እንዲያደርግ እና ከሟቾች አስከሬን ንክኪ እንዲጠነቀቅ ነው ያሳሰቡት፡፡
የአለም ጤና ድርጅት እና የአፍሪካ ሲዲሲ አዲስ ተከሰተ ስለተባለው በሽታ መረጃው እንደደረሳቸው አስታውቀው የተላላፊነቱን ደረጃ ለመወሰን ከኮንጎ የጤና ተቋማት ጋር በቅርበት እየሰራን ነው ብለዋል፡፡
ከዚህ ባለፈም በሌሎች የሀገሪቱ ግዛቶች እና ጎረቤት ሀገራት ተመሳሳይ ምልክቶች የሚታይባቸው ሰዎች ከተገኙ በአፋጣኝ ሪፖርት እንዲደረግ ጠይቀዋል፡፡
በዝንጀሮ ፈንጣጣ ወረርሽኝ እየተሰቃየች በምትገኝው ዲአር ኮንጎ ከ47 ሺህ በላይ ሰዎች በወረርሽ ሲጠቁ ከ1 ሺህ በላይ ሰዎች በማዕከላዊ አፍሪካዊቷ ሀገር መሞታቸውን የዓለም ጤና ድርጅት መረጃ ያመላክታል፡፡