በዳኒ አልቬስ ላይ ያሟረተው ግለሰብ ክስ ይጠብቀዋል ተባለ
አልቬስ በእስር ቤት ራሱን አጥፍቷል በሚል በማህበራዊ ሚዲያዎች ሲሰራጭ የነበረው መረጃ ፍጹም ሀሰተኛ መሆኑን ቤተሰቦቹና ጠበቃው ገልጸዋል
የቀድሞው የባርሴሎና ተጫዋች በቀረበበት የአስገድዶ መድፈር ክስ የአራት አመት ተኩል እስራት ተቀጥቷል
ብራዚላዊው ተጫዋች ዳኒ አልቬስ የማህበራዊ ሚዲያ ሟርት ሰለባ ሆኗል።
በኤክስ (ትዊተር) በአንድ ግለሰብ የተጋራው “ዳኒ አልቬስ ራሱን ማጥፋቱን ሰምቻለሁ” የሚል አጭር መረጃ ከስፔን አልፎ መላውን አለም አዳርሷል።
“ፓውሎ አልቡቁርቂ” በሚል ቅጽል ስም የሚጠቀም የኤክስ ተጠቃሚ የተጋራው መረጃ ከ6 ሚሊየን በላይ ሰዎች ተመልክተውታል።
አስገራሚው ነገር ደግሞ ከ12 ሺህ በላይ ሰዎች መረጃዎን መውደዳቸው (ላይክ ማድረጋቸው)ና ከ6 ሺህ 200 በላይ ሰዎች ለሌሎች ማጋራታቸው ወይም ሪትዊት ማድረጋቸው ነው።
Informação que me chega é que o Daniel Alves se matou.
— Paulo Albuquerque (@Al_buquerq) March 9, 2024
የቀድሞው የባርሴሎና ተጫዋች በማረሚያ ቤት ራሱን አጥፍቷል የሚለው መረጃን በርካታ የማህበራዊ ትስስር ገጾች ማራገባቸው ያበሳጨው የአልቬስ ወንድም ኔይ ዝምታውን ሰብሮ መረጃውን አስተባብሏል።
ባለፈው ወር በባርሴሎና በእስር ላይ የሚገኘውን ወንድሙን በአካል ሄዶ እንደጠየቀው የገለጸው ኔይ፥ “ሰዎች ምን ያህል ክፉ ብንሆን ነው እንዲህ አይነት መረጃ የምናጋራው፤ የእስር ቅጣቱ አይበቃውም ወይ?” ሲል በኢንስታግራም ገጹ አጋርቷል።
“ከ70 እና 60 አመት በላይ እድሜ ያላቸው አባት እና እናቴን ምን ያህል እንደሚጎዳ አያስቡም” ሲልም የማህበራዊ ሚዲያው የሀሰት መረጃ አደገኛነትን አንስቷል።
የተጫዋቹ ጠበቃም ሀሰተኛ መረጃውን ያጋራውን ግለሰብ ለመክሰስ መዘጋጀቱን ገልጿል።
ሀሰተኛ መረጃውን ለመጀመሪያ ጊዜ በኤክስ ያጋራው ግለሰብ በበኩሉ ከስምንት ስአታት በኋላ በለቀቀው ማስተባበያ የሚመስል መረጃ “እኔ ጠፍቶ የነበረ ዳኔልዚንሆ አልቬስ የተሰኘ የአጎቴ ልጅ ራሱን ሳያጠፋ እንደማይቀር መረጃ ደርሶኛል ነው ለማለት የፈለኩት፤ ሰዎች ግን ከዳኒ አልቬስ ጋር አገናኙት” ብሏል።
የ40 አመቱ ብራዚላዊ በቀረበበት የአስገድዶ መድፈር ወንጀል ክስ ጥፋተኛ ተብሎ ባለፈው ወር በአራት አመት ተኩስ እስራት እና በ150 ሺህ ዩሮ ካሳ እንዲቀጣ መወሰኑ ይታወሳል።
የቀድሞው የባርሴሎና፣ ሲቪያ፣ ፒኤስጂ እና ጁቬንቱስ ተጫዋች ሁሉም ፊቱን ሲያዞርበት ኔይማር አለሁልህ ብሎታል፤ አልቬስ ለከሳሹ እንዲከፍል የተላለፈበትን የ150 ሺህ ዩሮ ካሳ እንደሚከፍል አስታውቋል።
ለባርሴሎና ከ400 ጊዜ በላይ የተሰለፈው አልቬስ ከካታላኑ ክለብ ጋር ስድስት የሊግ እና ሶስት የሻምፒዮንስ ሊግ ዋንጫዎችን አንስቷል። በኳታር በተካሄደው የአለም ዋንጫም የብራዚል ብሄራዊ ቡድን አባል እንደነበር ይታወሳል።