በጉዳት ምክንያት ቁልፍ ተጫዋቾቹ ከሜዳ የራቁበት አርሰናል ምሽት ላይ አስቶንቪላን ይገጥማል
ቡድኑ ባጋጠመው ተከታታይ ጉዳት የአጥቂ መስመሩ መሳሳቱን ተከትሎ ስፍራውን ለማጠናከር በመጪው የዝውውር መስኮት ተጫዋቾችን ሊገዛ ይችላል እየተባለ ነው

ከመድፈኞቹ በ4 ነጥብ ከፍ ብሎ የሚገኘው ሊቨርፑል የነጥብ ልዩነቱን ለማስፋት ምሽት 12 ሰዓት ላይ ከብሬንትፎርድ ጋር የሚያደርገውን ጨዋታ ማሸነፍ ይጠበቅበታል
አርሰናል የሰሜን ለንደን ደርቢ ድሉን ለማስቀጠል ዛሬ በፕሪምየር ሊጉ ምሽት 2፡30 ላይ አስቶንቪላን ይገጥማል፡፡
የሚኬል አርቴታ ቡድን በሳምንቱ አጋማሽ ቶተንሃምን 2-1 በማሸነፍ በሁሉም ውድድሮች ያላሸናፊነት ከተጓዘባቸው ሶስት ጨዋታዎች በኋላ ወደ አሸናፊነት ተመልሷል፡፡
ሊቨርፑል ለመጨረሻ ጊዜ ከኖቲንግሃም ፎረስት ጋር ባደረገው ጨዋታ 1-1 በሆነ አቻ ውጤት መለያየቱን ተከትሎ መድፈኞቹ ከሊጉ መሪ በአራት ነጥብ ብቻ ርቀው ይገኛሉ።
የሰሜን ለንደኑ ክለብ የዛሬውን ጨዋታ ማሸነፉ ከሊጉ መሪ ጋር ያለውን የነጥብ ልዩነት የሚያጠብበት ወይም ወቅታዊ ውጤቱን የሚያስቀጥልበት ወሳኝ ጨዋታ ቢሆንም የቁልፍ ተጫዋቾቹን አገልግሎት በጉዳት ምክንያት አያገኝም፡፡
ቡድኑ ረቡዕ ከቶተንሀም ጋር ከመጫወቱ በፊት ብራዚላዊው አጥቂ ጋበሬል ጄሱስ በጉልበቱ ላይ ባጋጠመው ጉዳት ለረጅም ጊዜ ከሜዳ እንደሚርቅ አስታውቋል፡፡
ብራዚላዊው አጥቂ ከረጂም ወራት በኋላ ወደ ጎል አግቢነት ቢመለስም በቅርቡ ያጋጠመው ጉዳት ቀዶ ጥግና የሚያስፈልገው መሆኑን ተከትሎ እስከ ውድድር ዘመኑ መጠናቀቂያ የመመለሱ ነገር አጠራጣሪ መሆኑን የእንግሊዙ ሜትሮ ጋዜጣ ዘግቧል፡፡
የጄሱስ ጉዳት ከቡካዮ ሳካ እና ኤታን ንዋኔሪ ቀጥሎ በአርሰናል የአጥቂ ስፍራ ላይ በጉዳት ምክንያት የተፈጠረውን ክፍተት የሚያባብስ ነው፡፡
እነኚህ ተጫዋቾች በሌሉበት ራሂም ስተርሊንግ የአርሰናል የመጨረሻዎቹን ሁለት ጨዋታዎች በቀኝ ክንፍ ቦታ ላይ ተሰልፎ የተጫወተ ሲሆን በዛሬው ጨዋታም በዚሁ ስፍራ ተሰልፎ ወደ ሜዳ ሊገባ እንደሚችል ይጠበቃል።
ከዚህ ባለፈም ቡድኑ በመጪው የዝውውር መስኮት የአጥቂ ስፍራውን የሚያጠናክሩለት ተጫዋቾችችን ለመግዛት ወደ ገበያ ሊወጣ ይችላል ነው የተባለው፡፡
በቶተንሀሙ ጨዋታ ላይ በተቀያሪ ወንበር ላይ የነበረው ገብርኤል ማርቲኔሊ ወደ ቋሚ አሰላለፍ ሊመለስ ይችላል፡፡
በተጨማሪም በጫና ውስጥ ያለው ካይ ሃቨርትዝ በመጀመሪያ አሰላፍ ውስጥ ከሚካተቱ ተጫዋቾች መካከል እንዱ ነው፡፡
ቡድኑ በአሁን ወቅት በአማካኝ ስፍራ ላይ ጉዳት አላስተናገደም በዚህም አርቴታ ከቶተንሃም ጋር የተከተለውን የጨዋታ አሰላለፍ እንደሚከተል ሚረር ጋዜጣ አስነብቧል፡፡
የዛሬው ጨዋታ በሊጉ ሰንጠረዥ አናት ላይ ለሚገኙት ሊቨርፑሎች እና ለተከታዩ አርሰናል ወሳኝ ነው፡፡
ከመድፈኞቹ በ4 ነጥብ ከፍ ብሎ የሚገኘው ሊቨርፑል የነጥብ ልዩነቱን ለማስፋት ምሽት 12 ሰዓት ላይ ከብሬንትፎርድ ጋር የሚያደርገውን ጨዋታ ማሸነፍ ይጠበቅበታል፡፡
ሊቨርፑል ተሸንፎ አርሰናል የሚያሸንፍ ከሆነ መድፈኞቹ የነጥብ ልዩነቱን ወደ አንድ ዝቅ በማድረግ ወደ መሪነት የሚያደርጉትን ግስጋሴ የሚያፋጣን ይሆናል፡፡