ሃማስ እና ፋታህ ጋዛን ከጦርነቱ በኋላ የሚመራ ኮሚቴ ለማቋቋም ተስማሙ
ሁለቱ የፍልስጤም ተቀናቃኝ ሃይሎች ከስምምነት ላይ የደረሱት በግብጽ አደራዳሪነት ነው
እስራኤል ከ2007 ጀምሮ ጋዛን ሲያስተዳድር የቆየው ሃማስ ጦርነቱ ሲጠናቀቅ ምንም አይነት ሚና እንዲኖረው እንደማትፈልግ ደጋግማ ገልጻለች
የፍልስጤም ተቀናቃኝ ሃይሎች የሆኑት ሃማስ እና ፋታህ ጋዛን ከጦርነቱ በኋላ የሚያስተዳድር ኮሜቴ ለማዋቀር ስምምነት ላይ ደረሱ።
ሃማስና የፕሬዝዳንት ማህሙድ አባሱ ፋታህ ፓርቲ ስምምነት ላይ የደረሱት በግብጽ አደራዳሪነት በተካሄደ ምክክር ነው።
በካይሮ በተካሄደው ድርድር ከ10 እስከ 15 የፓርቲ አባል ያልሆኑ ታዋቂ ግለሰቦችን ያካተተ ኮሜቴ እንዲቋቋም የሁለቱም ሃይሎች ተወካዮች ፊርማቸውን አኑረዋል ብሏል አጃንስ ፍራንስ ፕሬስ በዘገባው።
የኮሜቴው አባላት በኢኮኖሚ፣ ትምህር፣ ጤና፣ ሰብአዊ ድጋፍና መልሶ ግንባታ ልምድ ያካበቱ ይሆናሉ ይላል የስምምነት ሰነዱ።
ሃማስና ፋታህ ኮሚቴው ከግብጽ ጋር የሚዋሰነውንና በፍልስጤም በኩል የሚገኘውን የራፋህ መተላለፊያ እንዲያስተዳድር መስማማታቸውም ተዘግቧል።
የፋታህን ቡድን የመሩት የማርቲው ማዕከላዊ ኮሚቴ አባል አዛም አል አህመድ ዛሬ ወደ ራማላህ ተመልሰው ፕሬዝዳንት ማህሙድ አባስ በስምምነቱ ላይ ፊርማቸውን እንዲያኖሩ ያደርጋሉ።
የሃማስ ልኡክ በፖሊትቢሮ አባሉ ካሊል አል ሃያ መመራቱ የተገለጸ ሲሆን፥ ስምምነቱ ለፍልስጤም የነጻነት ትግል በትብብር ለመስራት በር ከፋች ነው ተብሏል።
እስራኤል ሃማስና ፋታህ ከስምምነት ላይ ደርሰውበታል ስለተባለው ኮሚቴ የማዋቀር ጉዳይ እስካሁን አቋሟን አልገለጸችም።
ሃማስን ሙሉ በሙሉ የመደምሰስ ፍላጎታቸውን በተደጋጋሚ የገለጹት ጠቅላይ ሚኒስትር ቤንያሚን ኔታንያሁ ቡድኑ የጋዛው ጦርነት ከተጠናቀቀ በኋላ ሰርጡን እንደማያስተዳድር መናገራቸው ይታወሳል።
ማህሙድ አባስ የሚመሩት ፋታህ ላይም እምነት ማጣታቸውን ሲገልጹ መደመጣቸን ዘናሽናል አስታውሷል።
ሃማስ እና ፋታህ ከአምስት ወራት በፊት በቻይና አደራዳሪነት የ17 አመታት ክፍፍላቸውን በማቆም ለፍልስጤም አንድነት በጋራ ለመስራት መስማማታቸው አይዘነጋም።
ለእስራኤል ነጻ ሀገርነት እውቅና መስጠት የማይፈልገውና በስድስት ቀናቱ ጦርነት በእስራኤል በሃይል የተያዙ ቦታዎች ተለቀው ነጻዋ ፍልስጤም ትመሰረታለች የሚለው ሃማስ ከእስራኤል ጋር የሰላም ስምምነት ከተፈራረመው የማህሙድ አባሱ ፋታህ ጋር ግንኙነቱ የሻከረ ነው።
በተለይ በፈረንጆቹ 2006 በተካሄደው ምርጫ ሃማስ ማሸነፉን ተከትሎም ዌስትባንክን ከሚያስተዳድረውና ፋታህ ከተቆጣጠረው የፍልስጤም አስተዳደር ጋር ልዩነቱ መስፋቱ ይታወሳል።
ሁለቱ ቡድኖች ተከታታይ ድርድር አድርገው የአንድነት መንግስት ለመመስረት መስማማታቸውም አይዘነጋም።
ስምምነቱ ሃማስ የፍልስጤም አስተዳደር ከእስራኤል ጋር የደረሰውን የሰላም ስምምነት እንዲያከብር የሚያደርግ ቢሆንም ለእስራኤል ሉአላዊ ሀገርነት እውቅና ያልሰጠበት በመሆኑ እስራኤልና አሜሪካ የአንድነት መንግስቱን እውቅና አንሰጠውም ብለው ኢኮኖሚያዊ ማዕቀቦችን ጥለው ነበር።
ይህም የሃማስና ፋታህ የአንድነት መንግስት በአጭር ጊዜ እንዲፈርስና ግጭት እንዲቀሰቀስ ምክንያት መሆኑ የሚታወስ ነው።
እስራኤልና ምዕራባውያን አጋሮቿ ሃማስን በሽብርተኝነት በመፈረጅ ዌስትባንክን ለሚያስተዳድረው ፋታህ ደግሞ አለማቀፍ እውቅና በመስጠት የፍልስጤም የነጻነት ትግልን በሁለት ጎራ ከፍለውታል በሚል ይወቀሳሉ።
በሀምሌ ወር የተፈረመው "የቤጂንግ ስምምነት" ሁለቱ ተቀናቃኞች የአመታት ቁርሿቸውን ለመፍታት የተግባቡበት ሲሆን፥ በካይሮ የተደረሰው ስምምነትም የዚህ ማሳያ ተደርጎ ተነስቷል።