ቱርክ የፕሬዝዳንት ኤርዶሃንን ንግግር ያቋረጡ ዘጠኝ ሰዎች አሰረች
ኤርዶሃን ባለፈው ሳምንት በኢስታንቡል ንግግር ሲያደርጉ "ቱርክ ለእስራኤል ነዳጅ መሸጧን ቀጥላለች" ያሉ ተቃዋሚዎች ንግግራቸውን አቋርጠዋቸዋል
የግለሰቦቹ መታሰር የመናገር ነጻነትን የሚጋፋ ነው ያሉ ፖለቲከኞችና የመብት ተሟጋቾች ተቃውሟቸውን እያሰሙ ነው
ቱርክ የፕሬዝዳንት ሬሲፕ ጣይብ ኤርዶሃን ንግግርን ያቋረጡ ተቃዋሚዎችን አሰረች።
የሀገሪቱ ፍርድ ቤት ፕሬዝዳንቱ ባለፈው ሳምንት በኢስታንቡል በቴሌቪዥን የሚተላለፍ ንግግር ሲያደርጉ ተቃውሞ አሰምተዋል የተባሉት ዘጠኝ ሰዎች እንዲታሰሩ ወስኗል።
ተቃዋሚዎቹ የኤርዶሃን መንግስት ከእስራኤል ጋር የንግድ ግንኙነቱን እንዳቋረጠ ቢገልጽም ለቴል አቪቭ ነዳጅ መሸጡን ቀጥሏል ሲሉ ተደምጠዋል።
የፕሬዝዳንቱ ከፍልስጤማውያን ጋር የወገነ የሚመስል ትርክት በተግባር እየታየ አይደለም ማለታቸውንም ሬውተርስ አስታውሷል።
"መርከቦች ወደ ጋዛ ቦምቦችን ጭነው እየተጓዙ ነው፤ ለዘር ጭፍጨፋ የሚውል ነዳጅ መላክዎን ያቁሙ" ሲሉም በጋራ ተቃውሟቸውን አሰምተዋል።
ፕሬዝዳንት ሬሲፕ ጣይብ ኤርዶሃን ለተቃዋሚዎቹ ቁጣ የተቀላቀለበት ምላሽ ሰጥተዋል።
"ልጆቼ የጽዮናውያን አፈቀላጤ አትሁኑ፤ ምንም እንኳን የእነሱ ድምጽ፣ አፍ እና አይን ለመሆን ብትሞክሩ አይሳካላችሁም" ብለዋቸዋል።
"በመላው አለም የሚገኙ ጽዮናውያን ጣይብ ኤርዶሃን በየትኛው ጎን እንደሚቆም ጠንቅቀው ያውቃሉ፤ እናንተ ግን እስካሁን ይህን የተረዳችሁ አይመስልም" ነው ያሉት።
ፖሊስ በአንካራ የኤርዶሃንን ንግግር ለማቋረጥ የሞከሩትን ግለሰቦች በቁጥጥር ስር ያዋላቸው ሲሆን፥ አቃቤ ህግ ፕሬዝዳንቱን በመሳድብና ህገወጥ የተቃውሞ ሰልፍ በማድረግ ክስ መስርቶባቸዋል።
የግለሰቦቹ መታሰር ከፖለቲከኞች እና የመብት ተሟጋቾች ተቃውሞ አስነስቷል።
የሪፐብሊካን ፒፕል ፓርቲ መሪው ኦርጉር ኦዜል "ፕሬዝዳንት ኤርዶሃንን የተቃወሙ ዘጠኝ ወጣቶች እንዲታስሩ የተላለፈው ውሳኔ የሀገሪቱ ዴሞክራሲ ምን ያህን እየወደቀ መሆኑን ያሳያል" ብለዋል።
ወጣቶቹ ሃሳባቸውን በነጻነት የመግለጽ መብት እንዳላቸው በመግለጽም በአፋጣኝ እንዲፈቱ ጠይቀዋል።
ኤርዶሃን እስራኤል እና ሃማስ በጋዛ ጦርነት ከጀመሩ ወዲህ በቴል አቪቭ ላይ የሰላ ትችት በማሰማት ይታወቃሉ።
አንካራ በጋዛ የሰብአዊ ቀውስ እንዲባባስ አድርጋለች ካለቻት እስራኤል ጋር ባለፈው አመት ግንቦት ወር ላይ የንግድ ግንኙነቷን ሙሉ በሙሉ ማቋረጧን መግለጿ ይታወሳል።
"እስራኤል እንጂ ሃማስ አሸባሪ አይደለም" በሚለው ንግግራቸው የሚወሱት ኤርዶሃን፥ በፍልስጤማውያን ላይ የሚፈጸመው ግፍ ከተባባሰ ሀገራቸው ጦሯን ልታዘምት እንደምትችል መናገራቸውም አይዘነጋም።