ግድያው ፕሬዝዳንት ቡሃሪ የሃገራቸውን ደህንነት ለማስጠበቅ ስኬታማ ስራ መስራታቸውን በገለጹ በቀናት ውስጥ የተፈጸመ ነው
በናይጄሪያ ሽፍቶች ከሰሞኑ በፈጸሙት ጥቃት 218 ሰዎች መገደላቸው ተነገረ፡፡
ናጄሪያውያኑ ከፈረንጆቹ ጥር 2 እስከ 8 ባሉት ቀናት ነው በተለያዩ የሃገሪቱ አካባቢዎች ታጣቂዎች በፈጸሙት ጥቃት የተገደሉት፡፡
ፕሬዝዳንት መሃመዱ ቡሃሪ በእርሳቸው የመሪነት ዘመን ናይጄሪያ ከመቼውም ጊዜ በላይ ደህንነቷ መረጋገጡን በተናገሩ በቀናት ውስጥ ነው ይህ የሆነው፡፡
ቦኮሃራምን በመሳሰሉ የታጠቁ ቡድኖች የምትቸገረው ናይጄሪያ እገታ እና ግድያዎችን ጨምሮ ተደጋጋሚ ጥቃቶች ይፈጸሙባታል፡፡
ባለፈው ሳምንት በተለያዩ የሃገሪቱ አካባቢዎች በተፈጸሙ ጥቃቶች 218 ሰዎች መገደላቸውንም ነው የሃገሪቱ ብዙሃን መገናኛዎች የዘገቡት፡፡
ሽፍቶቹ 5 ያህል መንደሮችን ባወደሙበት ዛምፍራ ግዛት ከ200 በላይ ሰዎች መገደላቸውንም፤ ትናንት ቅዳሜ ስርዓተ ቀብራቸው ተፈጸመ ያለው ፕሪሚዬም ታይምስ ዘግቧል፡፡
ጥቃት ፈጻሚዎቹ መኖሪያ ቤቶችን ጨምሮ የወረሯቸውን አካባቢዎች አውድመዋል፡፡ ከ10 ሺ የሚልቁ ሰዎች ቤት አልባ ከመሆንም በላይ ለመፈናቀል መዳረጋቸውም ነው የተነገረው፡፡
ግድያውን ያወገዙት ፕሬዝዳንት ቡሃሪ በድርጊቱ ማዘናቸውን ገልጸው፤ ወንጀለኞቹን አነፍንፈን እስከምናጠፋቸው ታገሱን ሲሉ ለተጎጂዎች መልዕክት አስተላልፈዋል፡፡
የሃገሪቱ ጦር ታጣቂዎቹን እንደሚያጠፋም ነው ፕሬዝዳንቱ የተናገሩት፡፡ ሆኖም ድርጊቱ በቡሃሪ እና በመንግስታቸው ላይ ከፍተኛ ውግዘትን አስከትሏል፡፡