በናይጄሪያ አንድ ት/ቤት በታጣቂዎች በተከፈተ የተኩስ እሩምታ “150 ተማሪዎች ታግተው ደብዛቸው እንደጠፋ” ተገለጸ
ፖሊስ የትምህርት ቤቱ ጠባቂዎችን እና ሴት አስተማሪዎች ጨምሮ እስካሁን 26 ሰዎች መታገታቸው ይፋ አድርጓል
ከታህሳስ ወር ወዲህ በናይጄሪያ 1 ሺህ የሚጠጉ ተማሪዎች መታገታቸውንና 150ዎቹ ደብዛቸው እንደጠፋ መረጃዎች ያመላክታሉ
ታጣቂዎች በናይጄሪያ ካዱና ግዛት በሚገኝ አዳሪ ትምህርት ቤት ተኩስ መክፈታቸውን ተከትሎ 150 ተማሪዎች ደብዛቸው መጥፋቱን የትምህርት ቤቱ አስተዳደርና ወላጆች ገለጹ፡፡
ፓሊስ ከወታደራዊ አካላት ጋር በመሆን ፍለጋውን አጠናክሮ እየቀጠለ መሆኑን አስታውቀዋል፡፡
ከታህሳስ ወር ወዲህ ተማሪዎቻቸው በብዛት በታጣቂዎች ከታገቱባቸው የናይጄሪያ ትምህርት ቤቶች የአሁኑ የቤቴል ባፕቲስት ሁለተኛ ደረጃ አዳሪ ትምህርት ቤት አስረኛ መሆኑ ነው፡፡
ታጣቂዎቹ ተማሪዎቹን ካገቱ በኋላ በገንዘብ የመደራደር ባህርይ እንዳላቸውም ነው የአካባቢው ባለስልጣናት የሚገልጹት፡፡
በእገታው የተጨነቁ ወላጆች ልጆቻቸውን ፍለጋ በትምህርት ቤቱ ቅጥር ግቢ ተሰባስበው በታጋቾች እጅ የሚገኙ ልጆቻቸውን ክፉ እንዳይነካቸው አምላካቸውን እየለመኑ ይገኛሉ፡፡
ፖሊስ የትምህርት ቤቱ ጠባቂዎችን እና ሴት አስተማሪዎች ጨምሮ እስካሁን 26 ሰዎች መታገታቸው ይፋ አድርጓል፡፡
25 ተማሪዎች ከአጋቾች እጅ ማምለጥ እንደቻሉ ለሮይተርስ የተናገሩት ደግሞ የትምህርት ቤቱ መስራች ጆን ሃያብ ናቸው፡፡
እገታውን ተከትሎም የካዱና ግዛት ባለስልጠናት የቤቴል ባፕቲስት ሁለተኛ ደረጃ አዳሪ ትምህርት ቤትን ጨምሮ በአካባቢው የሚገኙ 12 ትምህርት ቤቶች እንዲዘጉ አድርጓል፡፡
የአሁኑ የቤቴል ባፕቲስት ሁለተኛ ደረጃ አዳሪ ትምህርት ቤት 180 ተማሪዎች ተቀብሎ በማስተማር ላይ የሚገኝ ትምህርት ቤት ነው፡፡
ከታህሳስ ወር ወዲህ በናይጄሪያ 1 ሺህ የሚጠጉ ተማሪዎች የታገቱ ሲሆነ ከታገቱት 150ዎቹ እስከሁን ያሉበት ሳይታወቅ ደብዛቸው እንደጠፋ መረጃዎች ያመላክታሉ፡፡
ከትምህርት ቤቶች በተጨማሪ ዋና ዋና መንገዶች፣ የግል መኖርያ ቤቶች እና ሆስፒታሎች ታጣቂዎች ዓላማ የሚያደርጓቸው ዋና ዋና ስፍራዎች ናቸው፡፡
ፕሬዝዳንት ሙሃመድ ቡሃሪ ባሳለፍነው የካቲት የክልል መንግስታት ለሽፍቶች የሚያደርጉትን የዓይነት ማበረታቻ ተችተው ፖሊሲያቸውን እንዲገመግሙ አሳስበው ነበር፡፡
ሁኔታው ለጡረተኛው የጦር ጄነራል ራስ ምታት መሆኑንም ነው ሮይተርስ በዘገባው ያተተው፡፡