አማጺያኑ የአየር ኃይል አውሮፕላን መተው እንደነበር ይታወሳል
የናይጄሪያ ጸጥታ ኃይሎች በሰሜን ምዕራብ የሀገሪቱ ክፍል በአጋቾች ስር የነበሩ 187 ሰዎችን ማስለቀቁን አስታወቀ፡፡
ዛምፋራ በተባለው የሀገሪቱ ግዛት የፖሊስ ባለስልጣናት እንዳሉት ጠላፊዎቹን ድርጊት ለማክሸፍ በተደረገ ዘመቻ ሰዎቹን ማስለቀቅ እንደተቻለ ገልጸዋል፡፡ ግዛቲቱ ከባለፈው ታህሳስ ጀምሮ ከባድ መሳሪያ የያዙ ታጣቂዎች ማዕከል የነበረች ሲሆን በዚህም ትምህርት ቤቶች፤ መንደሮች እና ሌሎችም ሰለባ እንደነበሩ ሮይተርስ ዘግቧል፡፡ በዛምፋራ ከባለፈው ዓመት ጀምሮ መንግስት የቴሌኮሙኒኬሽን አገልግሎትን መዝጋቱ የሚታወስ ነው፡፡
አጋቾች ሴቶችን እና ህጻናትን ከአራት አካባቢች አግተው ለሳምንታት ማቆየታቸው የሚታወስ ሲሆን አሁን የሀገሪቱ የጸጥታ ኃይሎች በወሰዱት ተልዕኮ ማስለቀቅ መቻሉን ነው የሀገሪቱ መንግስት ያስታወቀው፡፡
የዛምፋራ ግዛት ፖሊስ ቃል አቀባይ መሐመድ ሼሁ የፖሊስና ደህንነት ኤጄንሲዎች የአጋቾችን መገኛዎች በማሰስ ተልዕኮውን መወጣቱን ተናግረዋል፡፡
የታጠቁ አማጺያን የመከላከያ ቦታዎችን ማጥቃት፤ ሰዎችን ከእስር መልቀቅና የአየር ኃይል አውሮፕላን መጣልና የመሳሰሉትን ተግባራት መፈጸማቸውም ተጠቅሷል፡፡ የዛምፋራ ግዛት አጎራባች አካባቢዎች እነዚህ አማጺያን በየግዛቶቻቸው እየገቡ መሆኑን እየተናገሩ ነው ተብሏል፡፡