ከእስያ ወደ ሌሎች የአለማችን ክፍሎች እየተዛመተ ያለው “ሂኪኮሞሪ” - ከቤት የመውጣት ፍርሃት
በጃፓን፣ ደቡብ ኮሪያ እና ሆንግ ኮንግ ከ1 ነጥብ 5 ሚሊየን በላይ ሰዎች ከቤታቸው መውጣት ካቆሙ ወራት ወይም አመታት ሆኗቸዋል
በአሜሪካ፣ ስፔንና ፈረንሳይም የውጭውን አለም የፈሩ “የከተማ መናኞች” ቁጥር እየጨመረ ነው ተብሏል
የእስያ ሀገራትን ሲፈትን የቆየው “ሂኪኮሞሪ” ወደሌሎች የአለማችን ክፍሎችም እየተዛመተ ነው ተባለ።
ከማህበረሰቡ ጋር መቀላቀልን ፈርተው በቤታቸው የተደበቁ ሰዎች በጃፓንኛ “ሂኪኮሞሪ” እየተባሉ ይጠራሉ።
በጃፓን ለመጀመሪያ ጊዜ የታየው ችግር አሁን ወደ አሜሪካ፣ ስፔንና ፈረንሳይም መዛመቱን ሲኤንኤን ዘግቧል።
የየል ዩኒቨርሲቲ ጥናት የኢንተርኔት መስፋፋትና ከሰዎች ጋር የገጽ ለገጽ ግንኙነት እየላላ መሄድ ለ“ሂኪኮሞሪ” መንሰራፋት ምክንያቶች ናቸው ብሏል።
የኮቪድ 19 ወረርሽኝን ተከትሎ ሰዎች ከቤታቸው እንዳይወጡ መታዘዙም የውጭውን አለም የሚፈሩ “የከተማ መናኞች” ቁጥር እንዲጨምር ማድረጉን ነው ጥናቱ የሚያሳየው።
ጃፓንን ጨምሮ የተለያዩ የእስያ ሀገራት ከማህበረሰቡ መቀላቀል የፈተናቸውን ዜጎቻቸውን ወደቀደመ ህይወታቸው ለመመለስ ከፍተኛ በጀት መድበው እየሰሩ ነው።
ሀገራቱ ችግሩ የህዝብ ቁጥራቸው እንዲያሽቆለቁል አንዱ ምክንያት መሆኑን ያምናሉ።
በአለማቀፍ ደረጃ ምን ያህል በ“ሂኪኮሞሪ” የተጠቁ ሰዎች እንዳሉ እስካሁን በይፋ አልተገለጸም የሚለው ሲኤንኤን፥ በጃፓን፣ ደቡብ ኮሪያ እና ሆንግ ኮንግ ከ1 ነጥብ 5 ሚሊየን በላይ ሰዎች ከቤታቸው ከወጡ ወራትና አመታት ማስቆጠራቸውን ዘግቧል።
በሆንግ ኮንግ ዩኒቨርሲቲ ተባባሪ ፕሮፌሰሩ ፖል ዎንግ እንደሚሉት በከተማዋ ከ50 ሺህ በላይ ሰዎች በራቸውን ዘግተው ወደ ውጭ መውጣት ያቆሙ ከ50 ሺህ በላይ ሰዎች እንዳሉ ይገመታል።
አብዛኞቹ የችግሩ ተጠቂዎችም የአንደኛና ሁለተኛ ደረጃ ተማሪዎች መሆናቸውን ይገልጻሉ።
በጃፓንም 1 ነጥብ 5 ሚሊየን የሚጠጉ ሰዎች ከቤት መውጣት አስፈርቷቸው ለወራትና አመታት ደጁን ማየትና ማህበራዊ ህይወት መጀመር እንዳልፍደፈሩ በቅርቡ የሀገሪቱ መንግስት ያወጣው መረጃ ያሳያል።
የጃፓኑ ችግር ከሆንግ ኮንጉ የሚለየው ተማሪዎችና ታዳጊዎች ብቻ ሳይሆኑ ከስራ የሚሰናበቱና እድሜያቸው የገፋ ኑሮ ከበደን ያሉ ሰዎችም በ“ሂኪኮሞሪ” መጠቃታቸው ነው።
የተወሰኑ በ80ዎቹ የሚገኙ ወላጆችም ከመኝታ ክፍላቸው አልወጣ ያሉ በ50ዎቹ የእድሜ ክልል የሚገኙ ልጆቻቸውን ለመጦር መገደዳቸውም የችግሩን አሳሳቢነት ያሳያል ነው የተባለው።
ጃፓናውያን ሰዎች እያንዳንዱን ነገር በራሳቸው ብቻ መፈጸም እንዳለባቸውና ለሌሎች ግድ እንዳይኖራቸው የሰረጸው ባህል የማህበራዊ ህይወት ላይ ተጽዕኖው ጉልህ መሆኑን በክዩሹ ዩኒቨርሲቲ ተባባሪ ፕሮፌሰሩ ታካሂሮ ካቶ ይናገራሉ።
በተለይ ወንዶች የራሳቸውንና የቤተሰባቸውን ህይወት የመምራት ከፍተኛ ሃላፊነት የተጣለባቸው መሆኑና ከማንም ድጋፍ እንዳይጠብቁ የሚያደርገው ባህል ያሰቡት ያልተሳካላቸው በራቸውን ዘግተው እንዲገለሉ እያደረገ መሆኑ ተገልጿል።
ሲኤንኤን በ“ሂኪኮሞሪ” ወይም ማህበረሰቡን ፈርቶ ከቤት ያለመውጣት ችግር የተጠቁ ሰዎች አነጋግሮ በሰራው ዝርዝር ዘገባ፥ የወላጆች ከልጆቻቸው አብዝቶ የመጠበቅ፣ ከምክር ይልቅ እርምጃን መምረጥ፣ የላላ የማህበራዊ ህይወትና የኑሮ ጫና “የከተማ መናኞች” እንዲበራከቱ ማድረጉ ነው የተጠቆመው።