ጃፓን ሴቶች በወር አበባ ወቅት የሚሰማቸውን ህመም ወንዶች እንዲያውቁት የሚያደርግ ቴክኖሎጂ ሰራች
ቴክኖሎጂውን የተገጠመላቸው ወንዶች መራመድ እንዳልቻሉ ተናግረዋል
መሳሪያውን የሰራው ኩባንያ ወንዶች የሴቶች ህመም እንዲያውቁት ለማድረግ ቴክኖሎጂውን እንደሰራ አስታውቋል
ጃፓን ሴቶች በወር አበባ ወቅት የሚሰማቸውን ህመም ወንዶች እንዲያውቁት የሚያደርግ ቴክኖሎጂ ሰራች።
የዓለም ሴቶች ቀንን አስመልክቶ የጃፓን ቴክኖሎጂ ኩባንያ ሴቶች የወር አበባቸውን በሚያዩበት ወቅት የሚሰማቸውን የህመም ስሜት የሚያሳይ ቴክኖሎጂውን ይፋ አድርጓል።
በናራ የሴቶች ዩንቨርስቲ እና ኦሳካ በተሰኘ የቴክኖሎጂ ኩባንያ የተሰራው ፔሮኖይድ የተሰኘው ይህ ቴክኖሎጂ በወንዶች ሆድ ላይ እንዲገጠም ተደርጎ በወር አበባ ወቅት በሴቶች ላይ የሚደርሱ ህመሞችን ያስተላልፋል።
ቴክኖሎጂው በወር አበባ ወቅት የሚደርሱ የሆድ ቁርጠት እና ተያያዥ ህመሞች ጋር አቻ የሆነ ህመምን እንደሚያስተላልፍም ተገልጿል።
በበጎ ፈቃደኛ ወንዶች ላይ የተሞከረው ይህ ቴክኖሎጂ ወንዶቹ ለተወሰኑ ደቂቃዎች ህመሙ ከባድ እና የሚታገሱት እንዳልሆነ ተናግረዋል።
የ26 ዓመቱ ወንድ ወጣት እንዳለው በህመሙ ምክንያት መነሳት እና መራመድ አልቻልኩም ሲል ለሮይተርስ ተናግሯል።
ሴቶች በየወሩ በወር አበባ ወቅት ከህመማቸው ጋር እየታገሉ ስራ እንደሚሰሩ ወንዶች ሊያውቁ እና ህመማቸውን ሊረዱ ይገባልም ተብሏል።
በጃፓን ያሉ አሰሪ ተቋማት ሴቶች በወር አበባ ወቅት ፈቃድ የመውሰድ እና ክፍያ የማግኘት መብት የሚፈቅድ ህግ ቢኖርም ብዙ ሴቶች ግን ይህን መብት በተለያዩ ጫናዎች ምክንያት አይጠቀሙትም ተብላል።