የጃፓን የህዝብ ቁጥር ሲያሽቆለቁል የውጭ ሀገር ነዋሪዎች ክብረ ወሰን ተሻገረ
ለመጀመሪያ ጊዜ የጃፓን ነዋሪዎች ቁጥር በሁሉም 47 ግዛቶች አሽቆለቆለ
ጠቅላይ ሚንስትር ፉሚዮ ኪሺዳ የወሊድ ምጣኔን መቀልበስ ቀዳሚ አጀንዳ አድርገዋል
የጃፓን ህዝብ ቁጥር ከመቼውም ጊዜ በበለጠ በፍጥነት እየቀነሰ ነው ተብሏል።
የውጭ ሀገር ነዋሪዎች ቁጥር ደግሞ ወደ ሦስት ሚሊዮን በመድረስ ክብረ ወሰን ማለፉን የመንግስት መረጃዎች አመልክተዋል።
መረጃው እንደሚያሳየው የጃፓን ማህበረሰብ በመላ ሀገሪቱ በእርጅና ላይ እንደሚገኝ እና የውጭ ዜጎች እየቀነሰ የመጣውን የህዝብ ቁጥር በማካካስ ረገድ ትልቅ ሚና እየተጫወቱ ነው።
ከጥር 2023 ጀምሮ በሀገር ውስጥ ጉዳይ እና ኮሙኒኬሽን ጉዳዮች ሚንስቴር የተለቀቀው የነዋሪዎች ምዝገባ መረጃ መሰረት፤ የጃፓን ዜጎች ቁጥር ለ14ኛ ዓመት በ800 ሽህ ቀንሷል። ይህም የሀገሪቱን ህዝብ ቁጥር ወደ 122.42 ሚሊዮን አድርሷል።
ለመጀመሪያ ጊዜ የጃፓን ነዋሪዎች ቁጥር በሁሉም 47 ግዛቶች አሽቆልቁሏል ሲል መረጃው አመልክቷል።
በጃፓን የሚኖሩ የውጭ ሀገር ዜጎች ቁጥር 2.99 ሚሊዮን የደረሰ ሲሆን፤ ይህም ካለፈው ዓመት ጋር ሲነጻጸር በ10 ነጥብ 7 በመቶ ብልጫ አለው።
ሮይተርስ እንደዘገበው በ2008 ዝቅተኛ የወሊድ መጠን ምክንያት የህዝቡ ቁጥር በየዓመቱ የቀነሰ ሲሆን፤ ባለፈው ዓመት ዝቅተኛ ደረጃ ላይ ደርሷል።
መንግስት ችግሩን ለመፍታት በርካታ ሴቶችን መቅጠር ጨምሮ የተለያዩ መንገዶችን ለመጠቀም አልሟል።
"የተረጋጋ የሰው ኃይልን ለማረጋገጥ መንግስት የሴቶችን፣ አረጋውያንን እና ሌሎችን የስራ ስምሪት ለማሳደግ ማሻሻያዎችን ያበረታታል" ሲሉ ዋና የካቢኔ ጸሀፊ ሂሮካዙ ማትሱኖ ተናግረዋል።
ጠቅላይ ሚንስትር ፉሚዮ ኪሺዳ የወሊድ ምጣኔን መቀልበስ ቀዳሚ ጉዳይ ያደረጉ ሲሆን፤ መንግስታቸው ከፍተኛ እዳ ቢኖርበትም፤ በዓመት 25 ቢሊዮን ዶላር ለህጻን እንክብካቤ እና ለወላጆች ድጋፍ አቅዷል።