የደቡብ ኮሪያ ህዝብ ቁጥር በ75 አመት ውስጥ በግማሽ ሊቀንስ ይችላል ተባለ
የአለማችን ዝቅተኛውን የውልደት ምጣኔ ክብረወሰን የያዘችው ሴኡል በ2023ም የራሷን ሪከርድ አሻሽላለች
ደቡብ ኮሪያ መውለድን ለማበረታታት ወጪ ያደረገችው 270 ቢሊየን ዶላር በላይ የህዝብ ቁጥሯን ከማሽቆልቆል ሊታደገው አልቻለም
እስያዊቷ ሀገር ደቡብ ኮሪያ ከሚወለደው ይልቅ የሚሞተው እየበዛባት የህዝብ ቁጥሯ እየቀነሰ ይገኛል።
ሀገሪቱ በራሷ የተያዘውን የአለማችን ዝቅተኛ የውልደት ምጣኔ በ2023 ማሻሻሏም ተገልጿል።
አንዲት ደቡብ ኮሪያዊ ሴት በህይወት ዘመኗ ልትወልደው የምትችለው ህጻን በ2022 ከነበረበት 0.78 በ2023 ወደ 0.72 ዝቅ ብሏል።
የደቡብ ኮሪያ ህዝብ ቁጥር ሳይቀንስ ባለበት እንዲቀጥል የአንዲት ሴት የውልደት ምጣኔ 2 ነጥብ 1 መሆን አለበት የሚለው የሀገሪቱ ስታስቲክስ ቢሮ፥ ባለፉት ሰባት አመታት የተመዘገበው ግን ከዚህ በብዙ እንደሚርቅ አመላክቷል።
ይህም ሀገሪቱን ባለፉት አራት ተከታታይ አመት የህዝብ ቁጥሯ እንዲቀንስ ማድረጉን ነው የጠቆመው።
የወልርልዶ ሜትር መረጃ እንደሚያሳየው በ2023 የደቡብ ኮሪያ ህዝብ ቁጥር 51 ሚሊየን 784 ሺህ ነበር፤ አሃዙ ከ2022 ጋር ሲነጻጸር በ31 ሺህ ያነሰ ነው። በ2024ም የሀገሪቱ ህዝብ ቁጥር ከ2023ቱ እንደሚቀንስ ነው ስታስቲካዊ መረጃዎች የሚያሳዩት።
የውልደት ምጣኔው በዚሁ ከቀጠለ የእስያዊቷ ሀገር የህዝብ ቁጥር በ21ኛው ክፍለዘመን ማብቂያ በግማሽ ይቀንሳል ተብሎ ይጠበቃል ብሏል ሬውተርስ በዘገባው።
በ50 አመታት ውስጥ ለስራ ብቁ የሆነ የሀገሪቱ ህዝብ ቁጥር በግማሽ ይቀንሳል፤ በአስገዳጅ ወታደራዊ አገልግሎት የሚሳተፉ ወጣቶች ቁጥርም በ58 በመቆ ይወርዳል። ከሀገሪቱ ህዝብ ከግማሽ በላዩ ከ65 አመት በላይ አዛውንት ሆኖ የትውልዱ መቀጠል አሳሳቢ ይሆናልም ነው የተባለው።
የውልደት ምጣኔው እያሽቆለቆለ መሄድ ያሳሰባት ሴኡል ከፈረንጆቹ 2006 ጀምሮ ከ270 ቢሊየን ዶላር በላይ መውለድን ለሚያበረታቱ ስራዎች ብታቀርብም ውጤት አላገኘችም።
የኑሮ ውድነት፣ የስራ ጫና እና ሴቶችን በወሊድ ወቅት የማያበረታታ ስርአት መፈጠሩ ደቡብ ኮሪያውያን አግብተው እንኳን መውለድ እንዳይፈልጉ ምክንያት መሆናቸው ይነገራል።
ጎረቤት ጃፓንም ወጣት ዜጋዋ ራሱን ሳይተካ ወደ እርጅና እየገሰገሰ ያለባት ሀገር ሆናለች፤ ቻይናም የውልደት ምጣኔዋ አሽቆልቁሎ የአለም የህዝብ ቁጥር መሪነቷን በህንድ መነጠቋ ይታወሳል።