የበሽር አል አሳድ የስደት ህይወት ምን ሊመስል ይችላል?
የአሳድ ቤተሰቦች በሩሲያ ከ40 ሚሊየን ዶላር በላይ የሚያወጡ መኖሪያ ቤቶችን አስቀድመው መግዛታቸው ተነግሯል

የአሜሪካ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር አሳድ እና ቤተሰቦቻቸው ከ2 ቢሊየን ዶላር በላይ ሀብት ማካበታቸውን መግለጹ ይታወሳል
የቀድሞው የሶሪያ ፕሬዝዳንት በሽር አል አሳድ በሩሲያ ጥገኝነት አግኝተው የስደት ህይወትን አሃዱ ብለዋል።
አል አሳድ በጥድፊያ ህይወታቸውን ለማትረፍ ሲጉዙ ቅንጡ መኪናዎችና ወርቆችን ጨምሮ በርካታ ሀብቶችን መዘንጋታቸውን አማጺያኑ ደማስቆን ሲቆጣጠሩ ያገኙት ዋሻ ምስክር ሆኗል።
በወንድማቸው ቤት ስር የተገነባውና ከፍተኛ ዋጋ ያላቸው ንብረቶች የተከማቹበት ዋሻ በሽር አል አሳድ ወደ ሞስኮ ሲኮበልሉ ከለላ ሆኗቸዋል።
ይሁን እንጂ የቀድሞው ፕሬዝዳንት ወደ ሞስኮ ሲጓዙ ባዶ እጃቸውን እንደማይሆን ይገመታል። አስቀድመውም በልጆቻቸውና በተለያዩ ስማቸው ብቻ ባለ ሚስጥራዊ ድርጅቶች በቢሊየን የሚቆጠር ሀብት ማሸሻቸው ተነግሯል።
የአሜሪካ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር የአሳድ ቤተሰቦች ሀብት 2 ቢሊየን ዶላር እንደሚደርስ መገመቱን ዴይሊሜል አስታውሷል።
የሩሲያ መገናኛ ብዙሃንም በሞስኮ ይገኛሉ ያሏቸው በሽር አል አሳድ የስደት ህይወታቸው የቅንጦት መሆኑ እንደማይቀር የሚያመላክቱ ዘገባዎችን እያወጡ ነው።
የአሳድ ቤተሰቦች በሩሲያ መዲና ከ40 ሚሊየን ዶላር በላይ የሚያወጡ ቢያንስ 20 አፓርትመንቶችን መግዛታቸውን ፋይናንሽያል ታይምስ ዘግቧል።
አፓርትመንቶቹ የሞስኮ ሰማይ ጠቀስ ህንጻዎች የሚገኙባቸውና የሩሲያ ባለጠጋዎች፣ ሚኒስትሮችና ከፍተኛ ባለስልጣናት በሚኖሩባቸው አካባቢዎች የሚገኙ ናቸው ተብሏል።
ሶሪያን ለ24 አመታት የመሩት አሳድ በለንደን ከተወለዱት ባለቤታቸው አስማ አል አሳድ ሶስት ልጆችን አግኝተዋል፤ ሃፌዝ እና ካሪም የተባሉ ወንድ ልጆችና የ22 አመቷን ዜን።
የ24 አመቱ ሃፌዝ በሩሲያ የፒኤችዲ ትምህርቱን ሲከታተል የቆየ ሲሆን፥ አስማ አል አሳድ ባለቤቷ ከሶሪያ እንደወጣ ሁለት ልጆቿን ይዛ ወደ ሩሲያ መግባቷ ተዘግቧል።
ቤትን ለማስዋብ ከፍተኛ ገንዘብ በማፍሰስ ተደጋጋሚ ወቀሳ የሚቀርብባቸው ባለቤታቸው አስማ አል አሳድ በስደት የሚኖሩባቸውን መኖሪያ ቤቶች በማስዋብ እንደሚጠመዱ ይጠበቃል።
ዊክሊክስ በ2012 ይፋ ያደረገው መረጃ የአሳድ ባለቤት ቤተመንግስቱን ለማደስና ለማስዋብ 350 ሺህ ዶላር ወጪ ማድረጋቸውን ያሳያል።
በጦርነት በምትታመሰው ሀገር 7 ሺህ ዶላር የሚያወጣ ጫማ መጫማታቸውም ቁጣ መቀስቀሱ ይታወሳል።
መሀመድ ማክሉፍ የተባለው የአሳድ አጎት በሶሪያ ሁለተኛው ሀብታም ሰው እንደሆነ ይነገራል።
ግለሰቡ በሩሲያ ቅንጡ መኖሪያ ቤቶች እንዳሉት መገለጹም የበሽር አል አሳድ የስደት ህይወት የተደላደለ እንደሚሆን ሌላኛው ማሳያ ነው ተብሏል።
ክሬምሊን አሳድና ቤተሰቦቻቸው በፕሬዝዳንት ፑቲን ፈቃድ ጥገኝነት ማግኘታቸውን ቢገልጽም የት እንደሚገኙ ግን ከመናገር ተቆጥቧል።
ለደህንነታቸው ሲባል መንግስት በሚያዘጋጅላቸው መኖሪያ ቤት ይኖራሉ ወይስ ወደ ቅንጡ አፓርትመንቶቹ ይገባሉ የሚለውም እስካሁን ምላሽ አላገኘም።