የፖለቲካ ምህዳሩ የፖሊሲ ሙግት ለማቅረብ ይቅርና "ጦርነት ይቁም ብሎ ሰልፍ ለማድረግ" አያስችልም- አቶ ግርማ
ተቃዋሚ ፓርቲዎች መግለጫ ከማውጣት የዘለለ ተጽኖ የሌላቸው ደካሞች ናቸው የሚሉ ትችቶች ይሰነዘሩባቸዋል
የጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ አስተዳደር በአንጻሩ "የተፎካካሪ ፓርቲ" አባላትን በካቢኔ ውስጥ በማካተት ጭምር ምህዳሩ እንዲሰፋ በጎ እርምጃ መውሰዱን ይገልጻል
ኢትዮጵያ ከፓርቲ ጋር የተዋወቀችው በአቢዮታዊ ወታደራዊ መንግስት (ደርግ) ወቅት ቢሆንም በርከት ያሉ ተፎካካሪ ፖለቲካ ፓርቲዎች የተፈጠሩት በምርጫ ላይ የተመሰረተ ዴሞክራሲያዊ መንግስት መስርቻለሁ ካለችበት ከደርግ አስተዳደር ውድቀት በኋላ ነው፡፡
ላለፉት 3 አስርት አመታት በላይ በሚበልጡ ጊዜዎች እንደ ጊዜው እና ፖለቲካ ሁኔታው የፓርቲዎቹ እንቅስቃሴ እና ተጽእኖ ፈጣሪነት ከፍ እና ዝቅ እያለ እዚህ ደርሷል፡፡
ሆኖም ፓርቲዎች ምርጫ ሲደርስ ካልሆነ በቀር ከዛ በኋላ በሚኖሩ ጊዚያት የመንግስትን ፖሊሲ እና አቋም በመተቸት እንዲሁም በሀገራዊ ሁኔታዎች ላይ ጠንካራ ድምጽ በመሆን ረገድ ከፍተኛ ክፍተት አለባቸው የሚል ትችት ይቀርብባቸዋል።
በሀገሪቱ የፖለቲካ ፉክክር ታሪክ ውስጥ ከፍተኛ ግለት እና ሰፊ እንቅስቃሴ የነበረበት ተቃዋሚ ፓርቲዎችም ስልጣን ለመያዝ የሚያስችል ድምጽ አግኝተውበት የነበረው የ1997ቱ ምርጫ በታሪክ ከሚጠቀሱት መካከል ዋነኛው ነው ፡፡
የዚህን ምርጫ ውጤት ተከትሎ በተፈጠሩ አለመግባባቶች በገዥው መንግስት የወጡ አዳዲስ አዋጆች ተፎካካሪ ፓርቲዎች እንዲቀዛቀዙ ህዝቡም በፓርቲዎች ላይ ያለው እምነት እንዲሸረሸር ያደረገ ስለመሆኑ ይነገራል፡፡
ከ2010 ዓም ጀምሮ በስልጣን ላይ የሚገኘው የጠቅላይ ሚኒስትር አብይ (ዶ/ር) አስተዳደር በትጥቅ ትግል ላይ የነበሩትን ጨምሮ በተለያየ ሁኔታ በሀገር ውስጥ እና በውጭ የነበሩ ፓርቲዎችን በፖለቲካው መድረክ በማሳተፍ ምህዳሩ እንዲሰፋ አድርጊያለሁ ሲል ይናገራል፡፡
ከዚህ ባለፈም በመድብለ ፓርቲ ስርአት ተቀናቃኝ ፓርቲዎች በመንግስት አስተዳደር ውስጥ ሀላፊነት በመስጠት ስኬታማ ስራ መስራቱን ያነሳል፡፡
ነገርግን ህብር ኢትዮጵያ ፖርቲን ጨምሮ በርካታ የተቃዋሚ ፖርቲዎች የፖለቲካ ምህዳሩ አሁንም ጠባብ ነው ይላሉ።
በኢትዮጵያ ፖለቲካ ውስጥ ለረጅም ጊዜ የቆየ ተሳትፎ ያላቸው ፖለቲከኛ እና በአሁኑ ወቅት የህብር ኢትዮጵያ ፓርቲ ሊቀመንበር አቶ ግርማ በቀለ የፖለቲካ ምህዳሩ አይደለም የፓሊስ እና አዋጅ መመሪያዎችን ለመሞገት "ጦርነት ይቁም" ብሎ ሰልፍ ለማድረግ የማያስችል ነው ሲሉ ለአል ዐይን አማርኛ ተናግረዋል።
አቶ ግርማ “ቀደም ባለው ባለው ጊዜ የሚያሳስሩ ትችቶች እና የተለየ ሀሳብ የማራመድ ሁኔታዎች አሁን ላይ የሚያስገድሉ ሆነዋል፤ የተለየ ሀሳብ ማንጸባረቅ ከተለያዩ ቡድኖች ጋር አስፈርጆ እስር እና እንግልት የሚያስከትል ነው፤ ይህ ደግሞ በተፎካካሪዎች ብቻ ሳይሆን በገዥው ፓርቲ አባላት እና አመራሮች ላይ ተደርጎም አይተነዋል” ብለዋል፡፡
በተጨማሪም የሰላም መደፍረሶች እና በየቦታው የሚከሰቱ ግጭቶች የፓርቲ ስራንም ሆነ የአባላት ምልመላን ለማካሄድ ብሎም አማራጭ ፖሊስን ለማስተዋወቅ ፣ ህዝባዊ ስብሰባዎችን ለማድረግ እና ለመወያየት ሁኔታዎች አመቺ አለመሆናቸውን አቶ ግርማ ያክላሉ፡፡
“ሰላማዊ ሰልፍ በዴሞክራሲያዊ አስተዳደር ውስጥ ለዜጎች ከሚሰጡ መብቶች መካከል ትንሹ ነው፤ ቢሻሻል ፣ ቢቀየር ፣ ቢስተካከል ብለህ የምታስበውን በሙሉ መንግስት እንዲሰማለህ የምትጠይቅበት ድምጽህን የምታሰማበት መንገድ ነው፤ ነገር ግን ከሰላማዊ ሰልፍ አቅም እንኳን አሁን ላይ መንግስትን የሚደግፉ ካልሆኑ በስተቀር መንግስትን የሚተቹ እና የሚቃወሙ ሌላው ቀርቶ ሰላም እንዲሰፍን የሚጠይቁ ሰልፎችን ማከናወን ክልክል ሆኗል”፡፡
የህብር ኢትዮጵያ ፓርቲ ሊቀመንበር አቶ ግርማ በቀለ በእርግጥ የኢትዮጵያ ተፎካካሪ ፓርቲዎች የሚጠበቅባቸውን ያህል ተጽዕኖ ፈጥረዋል ብለው ባያስቡም ነገር ግን “የምንጫወተው ባለው ሜዳ ነው የምንሰራው ግን ሜዳውን ለማስተካከል ነው” ብለዋል፡፡
“የፖለቲካ ምህዳሩን በጋራ ለማሻሻል ፣የልዩነት ሀሳቦችን ለመቀበል እና ለማስተናገድ እንዲችል አድርገን ካልሰራነው በስተቀር የአንድ ፓርቲ አድራጊ ፈጣነት የሚጎላበት በተቃራኒው ተፎካካሪ ፓርቲዎች አሉ ከመባል ባለፈ አማራጭ የፖሊሲ ሀሳቦችን ይዘው ወደ ፊት የመምጣታቸውን እድል ከዚህ ይበልጥ እንዳይመናመነው ያሰጋኛል”፡፡
የኢትዮጵያ የፖለቲካ ፓርቲዎች የጋራ ምክር ቤት ሰብሳቢ አቶ ሰለሞን አየለ ወቅታዊ ሀገራዊ የፖለቲካ ሁኔታዎች ስለ ኢትዮጵያ ያገባኛል የሚሉ ሁሉን ያሳተፈ የጋራ ፖለቲካዊ መፍትሄ እንደሚሻው ያምናሉ፡፡
የከፋ አረንጓድ ፓርቲ ፕሬዝደንት የሆኑት የምክር ቤቱ ሰብሳቢ የፓርቲዎችን የአማራጭ የፖሊሲ አቅም እና አጠቃላይ ተጽዕኖ ፈጣሪነት ለመገምገም ሀገራዊ የፖለቲካ ምህዳሩ መስተካከል እንደሚገባውም አብራርተዋል፡፡
ሀገሪቱ የመድብለ ፓርቲ ስርአት እንደመከተሏ ወንበር አግኝተው ፓርላማ የገቡም ሆነ በተፎካካሪ ፓርቲነት እየተንቀሳቀሱ የሚገኙ ፓርቲዎች ድምጻቸውን ማሰማት የሚችሉበት መድረክ እንደሚያሻቸው ተናግረዋል፡፡
ሰብሳቢው “አጠቃላይ የማህበራዊ ፖለቲካዊ ሁኔታዎችን ከተመለከትን በኢኮኖሚውም በሰላሙም ትንሽ ውጥረት የነገሰበት ሁኔታ ላይ እንደምንገኝ መገንዘብ አይከብድም፤ የፖለቲካ እንቅስቃሴ ለማድረግ እና ለመቃወም በቅድሚያ ሀገራዊ ሁኔታዎች በተረጋጋ ሁኔታ ላይ ሊሆኑ ይገባል” ሲሉ አብራርተዋል፡፡
ሀገር የሁላችንም ናት የሚሉት አቶ ሰለሞን “ተቃራኒ ሀሳቦች በጠላትነት የሚስፈረጁ ሊሆኑ አይገባም ይልቁንስ በስልጣን ላይ የሚገኝው አካል በተለይም በእንደዚህ አይነት ሁኔታ ውስጥ በሚገኝበት ጊዜ ለተለዩ ሀሳቦች ጆሮ መስጠቱ ፖለቲካውን ለማረጋጋት እና መፍትሄ ለማመንጨት ሊያግዘው ይችላል” ባይ ናቸው፡፡
ከዚህ ባሻገር ግን ፓርቲዎች አማራጭ የፖሊሲ ሀሳቦችን አቅርቦ በህዝብ ዘንድ ተቀባይነት ለማግኝት ራሳቸውን ማጠናከር እንደሚጠበቅባቸው ተናግረዋል፡፡
“ተፎካካሪ የፖለቲካ ፓርቲዎች ከምርጫ በፊት ባሉት አመታት ከውስጥ ሽኩቻ ወጥተው በርዕዮተ አለም ፣ በፓርቲ አደረጃጀት እና በፓርቲ ፕሮግራም ላይ ጠንካራ ሆኖ መቅረብ ላይ ክፍተት አለባቸው እሱን ለማሻሻል የጋራ ምክር ቤቱ የተለያዩ እገዛዎችን እደረገ ነው” ብለዋል፡፡
ነዋሪነታቸውን በአሜሪካ ያደረጉት በኢትዮጵያ ፖለቲካ ፓርቲዎች እና የፖለቲካ እንቅስቃሴ ላይ ጥናት እና ምርምር የሚሰሩት አቶ ተስፋየ ወልደ ዩሀንስ አሁን ከፖለቲካ ሁኔታው ካለመመቸት በዘለለ የፖለቲካ ፓርቲዎች ምርጫን ብቻ እንደ መጨረሻ ግብ ወስዶ መሥራታቸው ለመዳከማቸው መነሻ እንደሆነ ያምናሉ፡፡
ከአመሰራረት ጀምሮ ልዩነት መፍጠር የሚችል ሀሳብ ወይም ርዕዮተ ዓለም ይዘው የሚነሱ ተቃዋሚ ፓርቲዎች አናሳ መሆናቸውን ይገልጻሉ፡፡
ከዚህ ባለፈም በውስጣቸው ያለ የሀሰብ መከፋፈልን ማስታረቅ አለመቻላቸው እንዲዳከሙ ፣ እንዲከስሙ አለፍ ሲልም እንዲፈርሱ ምክንያት ነው ብለዋል፡፡
በዚህ ውስጥ የመንግስት ጣልቃገብነት ቀላል እንዳልሆነም አቶ ተስፋየ ያነሳሉ፤ “መንግስት ስልጣን ማጋራት በሚለው አካሄድ የፓርቲዎች ልዩነት እንዲሰፋ አድርጓል። በፌደራል እና በክልል መንግስታት ውስጥ ሀላፊነት የተሰጣቸው የፓርቲ አባላት ፓርቲያቸው ከሚከተለው የፖለቲካ ርዕዮት በተለየ አለም ውስጥ ገብተው የመንግስትን ፖሊሲ እያስፈጸሙ ነው፤ ይህ እና ሌሎች መንግስት ተቃዋሚ ኃይሎች ላይ የሚያደርሰው ጫና እንዲከፋፈሉ እና አንድ ሆነው እንዳይቆሙ አድርጓል” ነው ያሉት
“እነዚህ በመንግስት ኃላፊነት ላይ ሹመት ያገኙ ግለሰቦች እና ፓርቲዎችም በቀደመው ልክ ለህዝብ ሲቆረቆሩ አልያም የመንግስትን አካሄድ ሲተቹ እምብዛም አይስተዋሉም፤ ይህም ህዝቡ በፓርቲዎች ላይ እምነት እንዲያጣ በፖለቲካ ስርአቱም ተስፋ እንዲቆርጥ እንዳደረገው” የስልጥና ምርምር እና ጥናት ባለሙያው ይናገራሉ፡፡
በተጨማሪም “ምንም እንኳን የፖለቲካ ፓርቲዎች የመጨረሻ ግብ ሀሳብ ሽጠው ተወዳድረው ስልጣን ለመያዝ ቢሆንም ከምርጫ በፊት ምን ሲሰሩ ቆዩ የሚለው መጠየቅ ያለበት ይመስለኛል፤ ህዝብን ማደረጃት ፣ የፓርቲ እና የአባላት አቅምን ማጠናከር በተመሳሳይ መንገድ ሄዶ ወደ ስልጣን ለመቅረብ ከመፈለግ ይልቅ ህዝቡ ምን ይፈልጋል ከሚል የመነጨ ከማህበረሰቡ ችግር የተቀዳ ፖሊሲ ማዘጋጀት ላይ ሊሰሩ እንደሚገባ” አቶ ተስፋየ አብራርተዋል፡፡
የገቡበት ፖለቲካ እስከሆነ ድረስ ለእስር እና ለህይወት መስዕዋትነትም ጭምር በመዘጋጀት ለውጥ ለማምጣት ቁርጠኘነቱ ከሌላቸው መኖራቸው ትርጉም አልባ ነው ያሉ ሲሆን፤ በዚህ ረገድ ጠንካራ ሆኖ ህዝብን ከኋላ ለማሰለፍ ተመሳሳይ ሀሳብ ያለቸው ተዋህደው ጠንካራ ሀብረት ሊፈጥሩ እንደሚገባ አመላክተዋል፡፡
ለዚህ የኢሀፓ እና የመኢሶንን የፖለቲካ እንቅስቃሴ የሚያነሱት የስልጠና ምርምር እና ጥናት ባለሙያው “በአምባገነናዊ ስርአት ውስጥም እንኳን ቢሆን እነዚህ ፓርቲዎች ከነስህተታቸው የነበራቸው ዝግጁነት፣ የፖለቲካ እውቀት እና የህዝብ ቅቡልነት አሁን ላይ ላሉ ፓርቲዎች ትምህርት የሚሆን ነው፤ ፓርቲዎች ከመግለጫ ያለፈ ተጽዕኖን በማሳደር የፖለቲካ ምህዳሩን መቀየር የሚፈልጉ ከሆነ ከመንግስትም ጫና በፊት የራሳቸውን አደረጃጀት እና መወቅር ሊፈትሹ ይገባል” ብለዋል፡፡