አሜሪካ ገመናዋን ለአለም ያጋለጠውን አሳንጄ ከብሪታንያ ለመቀበል እየተጠባበቀች ነው
የብሪታንያ ከፍተኛ ፍርድቤት የዊክሊክስ መስራቹ ለአሜሪካ ተላልፎ ይሰጥ ወይስ አይሰጥ በሚለው ዙሪያ ነገ የመጨረሻ ውሳኔ ያሳልፋል ተብሏል
ዋሽንግተን ምስጢራዊ መረጃዎቿን ይፋ ባደረገው ጁሊያን አሳንጄ ላይ 18 ክሶች እመሰርታለሁ ብላለች
የብሪታንያ ከፍተኛ ፍርድ ቤት የዊክሊክስ መስራቹ ጁሊያን አሳንጄ ለአሜሪካ ተላልፎ ይሰጥ ወይስ አይሰጥ በሚለው ጉዳይ በነገው እለት የመጨረሻውን ውሳኔ ያሳልፋል።
በለንደን የሚገኘው ፍርድቤት አሜሪካ አሳንጄን በሞት እንደማትቀጣ እና ክሱ በነጻነት የመናገር መብቱን ባከበረ መልኩ እንዲታይ ያቀረበችውን ማረጋገጫ ተመልክቶ ውሳኔ እንደሚያሳልፍ ነው ሬውተርስ የዘገበው።
የአሳንጄ የጠበቆች ቡድን አሳንጄ በ24 ስአት ውስጥ አትላንቲክን በአውሮፕላን ሊሻገር ወይም ከእስር ሊፈታ እንደሚችል ከመጥቀስ ውጪ የፍርድቤቱ ውሳኔ ምን ሊሆን እንደሚችል መገመት ይከብዳል ብለዋል።
በፈረንጆቹ 2006 ዊክሊክስ ድረገጽን የመሰረተው አውስትራሊያዊው ጁሊያን አሳንጄ አሜሪካን ጨምሮ የተለያዩ ሀገራት በሚስጢር የያዟቸውን ሰነዶች ለአለም ይፋ በማድረግ ይታወቃል።
አሜሪካ በአፍጋኒስታን እና ኢራቅ ካደረገቻቸው ጦርነቶች ጋር የተያያዙ በመቶ ሺዎች የሚቆጠሩ ሚስጢራዊ ሪፖርቶችን አውጥቷል።
በፈረንጆቹ 2010 የአሜሪካ ጦር ሄሊኮፕተር በኢራቅ መዲና ባግዳድ ሲቪሎችን ሲገድል የሚያሳይ ተንቀሳቃሽ ምስል መልቀቁም መነጋገሪያ እንደነበር አይዘነጋም።
የዊክሊክስ የመረጃ ምንተፋ “በአሜሪካ መከላከያ ታሪክ ግዙፉ የሚስጢራዊ ሰነዶች ስርቆት” ነው ያለችው ዋሽንግተን በጁሊያን አሳንጄ ላይ 18 ክሶችን ለመመስረት ከተዘጋጀችም አመታት ተቆጥረዋል።
የዊክሊክስ ድርጊት “ሃላፊነት የጎደለውና ብሄራዊ ደህንነቴን እንዲሁም ሚስጢራዊ መረጃዎች አቀባዮቼን አደጋ ላይ የጣለ ነው” በሚልም ብሪታንያ አሳንጄን አሳልፋ እንድትሰጣት ጥያቄ ስታቀርብ ቆይታለች።
የአሳንጄ የጠበቆች ቡድን ግን ዊኪሊክስ ላይ የወጡት ሚስጥራዊ ሰነዶች የአሜሪካን ጥፋት የሚያጋልጡ እና የህዝብን ጥቅም ያስጠበቁ ናቸው በማለት ይከራከራሉ።
በ2020 በብሪታንያ በቁጥጥር ስር የዋለው፤ በለንደን የኢኳዶር ኤምባሲ ውስጥ ለሰባት አመታት የቆየው፤ ከ2019 ጀምሮ በብሪታንያ ቤልመርሽ እስርቤት ውስጥ የሚገኘው አሳንጄ በዋሽንግተን በጥብቅ የሚፈለግ ቢሆንም በአለማቀፍ ደረጃ ቀላል የማይባሉ ደጋፊዎች አሉት።
የአሜሪካ ተላልፎ ይሰጠኝ ጥያቄና ክስ ጋዜጠኝነት የሚያዋርድና ሃሳብን በነጻነት የመግለጽ መብትን የሚቃረን ነው የሚሉ የሰብአዊ መብት ተሟጋቾችና የአውስትራሊያው ጠቅላይ ሚኒስትር አንቶኒ አልቤንዝ የ52 አመቱ ጋዜጠኛ እንዲፈታ በተደጋጋሚ ጠይቀዋል።
የብሪታንያ ፍርድ ቤት በ2021 ግለሰቡ ለአሜሪካ ተላልፎ እንዲሰጥ በይኖ የነበረ ሲሆን አሳንጄ ይግባኝ መጠየቁ የሚታወስ ነው።
የነገው የከፍተኛው ፍርድቤት ውሳኔም ለ13 አመት በእስርና ክስ ክርክር የቆየውን ጁሊያን አሳንጄ ቀጣይ እጣ ፈንታ የሚወስን ነው ተብሏል።