ብሪታኒያ ጁሊያን አሳንጅ ለአሜሪካ ተላልፎ እንዲሰጥ የተላለፈውን ውሳኔ አጸደቀች
አሜሪካ ወታደራዊ መረጃዎችን አሳልፎ ሰጥቶብኛል በሚል አሳንጅን እንደምትፈልገው ይታወቃል
የዊኪሊክስ መስራቹ አሳንጅ በ28 ቀናት ውስጥ ለአሜሪካ ተላልፎ ይሰጣል ተብሏል
በአሜሪካ በጥብቅ የሚፈለገው የዊኪሊክሱ መስራች ጁሊያን አሳንጅ ለአሜሪካ ተላፎ እንዲሰጥ የብሪታኒያ ፍርድ ቤት ባሳለፍነው ወርሃ መጋቢት 4 ቀን 2022 ውሳኔ ማሳለፉ አይዘነጋም፡፡
ይሁን እንጅ አሳንጅ ለአሜሪካ ፍርድ ቤት ተላልፎ እንዲሰጥ ፍርድ ቤቱ ያሳለፈው ውሳኔ ተፈጻሚ የሚሆነው የብሪታኒያ የሀገር ውስጥ ሚኒስቴር ሲያጸድቀው መሆኑ ተገልጾ ነበር፡፡
በዚህም መሰረት የብሪታኒያ የሀገር ውስጥ ጉዳይ ሚኒስትር ፕሪቲ ፓቴል፤ የብሪታኒያ መንግስት የዊኪሊክስ መስራች አሳንጄን ለአሜሪካ ተላልፎ እንዲሰጥ በፍርድ ቤት የተላለፈውን ውሳኔ ማጽደቃቸውን አስታውቀዋል፡፡
የፓቴል ውሳኔ ከአስር አመታት በላይ ሲካሄድ የነበረው የአውስትራሊያ ተወላጅ የአሳንጅ የህግና ፍርድ ሂደት ያበቃል ማለት እንዳልሆነ ተገልጿል፡፡
የብሪታኒያ መንግስት ውሳኔው ቢያጸድቀውም አሳንጅ አሁንም በ14 ቀናት ውስጥ ይግባኝ ማለትና ጉዳዩን ወደ ሰበር ሰሚ ችሎት መውሰድ እንደሚችል ተገልጿል፡፡
ነገር ግን ይግባኙ ውድቅ ከተደረገ፤ አሳንጅ በ28 ቀናት ውስጥ ለአሜሪካ ተላልፎ ሊሰጥ እንደሚችል ሮይተርስ ዘግቧል፡፡
የአሜሪካን ወታደራዊ እና ዲፕሎማሲያዊ መረጃዎች በማነፍነፍና በማተም እንዲሁም ወታደራዊ ሚስጥሮችን የያዙ ሰነዶችን ለውጭ ኃይሎች አሳለፎ ሰጥቷል በሚል በአሜሪካ ባለስልጣናት ጥርስ የተነከሰበት አሳንጅ 18 በሚሆኑ ጉዳዮች ተከሷል፡፡
ምንም እንኳ የ50 ዓመቱ አሳንጅ በአሜሪካ የቀረበለትን ክስ ውድቅ ቢያደርግም፤ አድርጎታል ከተባለው ድርጊት ጋር በተያያዘ ለ7 ዓመታት በለንደን በሚገኘው የኢኳዶር ኤምባሲ፤ እንዲሁም እንደፈረንጆቹ ከ2019 አንስቶ አስካሁን ድረስ በደቡብ ምስራቅ ለንደን በሚገኘው የቤልማርሽ እስር ቤት እንዲታሰር ምክንያት ሆኖታል።
በዚህም አውስትራሊዊው አሳንጅ መረጃ በመበርበርና በመሰለል ወንጀል ከተከሰሰ 10 ዓመታት አልፈዋል።
የአሜሪካ ባለስልጣናት አሳንጅን ተጠያቂ ያድርጉ እንጅ፤ ደጋፊዎቹ ግን አሳንጅ በአፍጋኒስታን እና ኢራቅ በተከሰቱ ግጭቶች የአሜሪካን ጥፋት በማጋለጡ ሰለባ የሆነ ሰው ነው ሲሉ ይከራከራሉ፡፡
በአሳንጅ ላይ እየሆነ ያለው ነገር በጋዜጠኝነት እና በነጻነት የመናገር መብት ላይ የተሰነዘረ ጥቃት ነው በሚል ክስ እስከ መመስረት የደረሱበት አጋጣሚም ነበር፡፡