የዊክሊክስ መስራቹ ጁሊያን አሳንጀ ከእስር ተለቆ ከብሪታንያ ወጣ
አሳንጀ አሜሪካ ካቀረበችበት 18 ክሶች አንዱን ለማመን የተስማማ ሲሆን በእስር ያሳለፋቸው አመታት ከግምት ውስጥ ገብተው በነጻ ይለቀቃል ተብሏል
ለ14 አመት የዘለቀው ውዝግብ በነገው እለት በፍርድ ቤት መቋጫ ያገኛል ተብሎ ይጠበቃል
የዊክሊክስ መስራቹ ጁሊያን አሳንጀ ከእስር ተፈትቶ ከብሪታንያ ለቆ መውጣቱ ተነገረ።
አሳንጀ በአሜሪካ ከቀረቡበት 18 ክሶች አንዱን ለማመንና የጥፋተኝነት ውሳኔ እንዲተላለፍ ከዋሽንግተን ጋር በተደረሰ ስምምነት ነው ከእስር የተለቀቀው።
የ52 አመቱ አውስትራሊያዊ የአሜሪካን ሚስጢራዊ መረጃዎች ለመመንተፍ በማሴርና ይፋ በማድረግ የቀረበበትን የወንጀል ክስ በነገው እለት ፍርድ ቤት ቀርቦ ያምናል።
ይህ ወንጀልም እስከ 62 ሳምንት የሚደርስ እስራት የሚያስቀጣ ሲሆን፥ አሳንጀ ግን በብሪታንያ በእስር ያሳለፈው ጊዜ ከግምት ውስጥ ገብቶ እንደሚለቀቅ ነው አሶሼትድ ፕረስ የዘገበው።
አሳንጀን ያሳፈረች የግል አውሮፕላን በታይላንድ መዲና ባንኮክ መድረሷ እየተዘገበ ሲሆን፥ ወደ ሰሜናዊ ማሪያና ደሴት ታመራለች ተብሏል።
የዊክሊክሱ መስራቹ ጁሊያን አሳንጀ ነገ ፍርድ ቤት ቀርቦ ነጻ ከተባለ በኋላም ወደ አውስትራሊያ እንደሚመለስ ነው የተጠቆመው።
አሳንጀ ማን ነው? የ14 አመት እስርና ውዝግቡስ?
በፈረንጆቹ 2006 ዊክሊክስ ድረገጽን የመሰረተው አውስትራሊያዊው ጁሊያን አሳንጀ አሜሪካን ጨምሮ የተለያዩ ሀገራት በሚስጢር የያዟቸውን ሰነዶች ለአለም ይፋ በማድረግ ይታወቃል።
አሜሪካ በአፍጋኒስታን እና ኢራቅ ካደረገቻቸው ጦርነቶች ጋር የተያያዙ በመቶ ሺዎች የሚቆጠሩ ሚስጢራዊ ሪፖርቶችን አውጥቷል።
በፈረንጆቹ 2010 የአሜሪካ ጦር ሄሊኮፕተር በኢራቅ መዲና ባግዳድ ሲቪሎችን ሲገድል የሚያሳይ ተንቀሳቃሽ ምስል መልቀቁም መነጋገሪያ እንደነበር አይዘነጋም።
የዊክሊክስ የመረጃ ምንተፋ “በአሜሪካ መከላከያ ታሪክ ግዙፉ የሚስጢራዊ ሰነዶች ስርቆት” ነው ያለችው ዋሽንግተን በጁሊያን አሳንጄ ላይ 18 ክሶችን ለመመስረት ከተዘጋጀችም አመታት ተቆጥረዋል።
የዊክሊክስ ድርጊት “ሃላፊነት የጎደለውና ብሄራዊ ደህንነቴን እንዲሁም ሚስጢራዊ መረጃዎች አቀባዮቼን አደጋ ላይ የጣለ ነው” በሚልም ብሪታንያ አሳንጀን አሳልፋ እንድትሰጣት ጥያቄ ስታቀርብ ቆይታለች።
በለንደን የኢኳዶር ኤምባሲ ውስጥ ለሰባት አመታት የቆየው፤ ከ2019 ጀምሮ በብሪታንያ ቤልመርሽ እስርቤት ውስጥ የቆየውና ዛሬ የተፈታው አሳንጀ በዋሽንግተን በጥብቅ ሲፈለግ ቢቆይም በአለማቀፍ ደረጃ ቀላል የማይባሉ ደጋፊዎች አሉት።
የአሜሪካ ተላልፎ ይሰጠኝ ጥያቄና ክስ ጋዜጠኝነት የሚያዋርድና ሃሳብን በነጻነት የመግለጽ መብትን የሚቃረን ነው የሚሉ የሰብአዊ መብት ተሟጋቾችና የአውስትራሊያው ጠቅላይ ሚኒስትር አንቶኒ አልቤንዝ የ52 አመቱ ጋዜጠኛ እንዲፈታ በተደጋጋሚ ሲወተውቱ ቆይተው ነበር።
የአሜሪካው ፕሬዝዳንት ጆ ባይደንም በሚያዚያ ወር አሳንጀ ላይ የቀረበው ክስ እንዲቋረጥ ከአውስትራሊያ የቀረበላቸውን ጥያቄ እያጤኑት መሆኑን መናገራቸው ይታወሳል።
ባለፈው ወርም የብሪታንያ ፍርድ ቤት የዊክሊክስ መስራቹ ለዋሽንግተን ተላልፎ መሰጠቱን በመቃወም ይግባኝ መጠየቅ እንዲችል መወሰኑ አይዘነጋም።
የሀገራትን ሚስጢራዊ መረጃ ማውጣት ለ14 አመታት በእስርና ክርክር ውስጥ ያቆየው ዊሊያም አሳንጀ በነገው እለት እፎይታን ያገኛል ተብሎ ይጠበቃል።