በመፈንቅለ መንግስት ወደ መንበር የመጡት ኮሎኔል ጎይታ የማሊ ጊዜያዊ ፕሬዝደንት ሆነው ቃለ መሀላ ፈጸሙ
ኮሎኔሉ ሁለት ጊዜ በፈጸሙት መፈንቅለ መንግስት ምክንያት ማሊ ከኢኮዋስ እና ከአፍሪካ ሕብረት ታግዳለች
ኮሎኔል ጎይታ ምርጫ እስከሚካሄድ ድረስ ጊዜያዊ ፕሬዝደንት ሆነው ይቀጥላሉ ተብሏል
ከዘጠኝ ወር በፊት የወቅቱ የማሊ ፕሬዘዳንት የነበሩትን አቡበከር ኬታን በመፈንቅለ መንግስትን ከስልጣን ያወረዱት ኮሎኔል አስሚ ጎይታ ዛሬ በይፋ የሀገሪቱ ጊዜያዊ ፕሬዝደንት ሆነው ቃለ መሀላ ፈጽመዋል።
የ38 ዓመቱ ኮሎኔል ጎይታ በማሊ ዲሞክራሲያዊ ምርጫ እስከሚካሄድ ድረስ የሀገሪቱ ጊዜያዊ ፕሬዝደንት ሆነው መሾማቸው ተገልጿል።
በምዕርብ አፍሪካዊቷ ሀገር ማሊ ባለፉት ዘጠኝ ወራት ውስጥ ሁለት ጊዜ ወታደራዊ መፈንቅለ መንግስት ተፈጽሟል። ሁለቱም መፈንቅለ መንግስቶች በ38 ዓመቱ ኮሎኔል አስሚ ጎይታ አስተባባሪነት የተፈጸሙ ናቸው።
ኮሎኔል ጎይታ ባሳለፍነው ነሀሴ ወር ላይ በወቅቱ የማሊ ፕሬዝደንት አቡበከር ኬታ ላይ በፈጸሙት መፈንቅለ መንግስት ስልጣን ቢቆጣጠሩም ፣ ከምዕራባዊያን እና አሜሪካ እንዲሁም ከአፍሪካ እና ሌሎች ዓለም አቀፍ ተቋማት ስልጣኑን ለሲቪል አስተዳደር እንዲሰጡ ከፍተኛ ጫና ከደረሰባቸው በኋላ እራሳቸውን ምክትል ፕሬዝደንት በማድረግ አዲስ ፕሬዝዳንት እና ጠቅላላ ሚንስትር እንዲሰየም አድርገው ቆይተዋል።
ይሁንና ከሳምንታት በፊት በድጋሚ ፕሬዝደንቱን እና ጠቅላይ ሚንስትሩን በማሰር እራሳቸውን የማሊ የሽግግር ጊዜ ፕሬዝደንት አድርገው ሾመዋል።
15 አባል አገራት ያሉት የምዕራብ አፍሪካ የኢኮኖሚ ማህበረሰብ (ኢኮዋስ) ሰሞኑን በጋና መዲና አክራ ከተማ በማሊ ወቅታዊ ጉዳዮች ዙሪያ መክሮ ነበር።
በዚህ ስብሰባ ላይ ኮሎኔል ጎይታ ስላካሄዱት መፈንቅለ መንግስት እና ስለ ቀጣይ እቅዳቸው ማብራሪያ የሰጡ ቢሆንም ፣ ኢኮዋስ በማሊ በተካሄደው የመጀመሪያው መፈንቅለ መንግስት ምክንያት በሀገሪቱ ላይ አስተላልፎት የነበረውን ከአባልነት የማገድ ውሳኔ በድጋሚ አራዝሟል።
ኢኮዋስን ተከትሎ የአፍሪካ ሕብረትም ከዚህ በፊት በማሊ ላይ ጥሎት የነበረውን ከአባልነት የማገድ ውሳኔ ፣ በማሊ በህዝብ ምርጫ የተመሰረተ መንግስት ስልጣን እስኪይዝ ድረስ አራዝሟል፡፡
ከዚህ በተጨማሪም ዓለም አቀፍ የፋይናንስ ተቋማት ለማሊ ወታደራዊ መንግስት ከሰብዓዊ መብት ጥበቃ ድጋፎች ባለፈ ሌሎች ድጋፎችን እንዳያደርጉም ህብረቱ አሳስቧል።
የዓለም ባንክም በአፍሪካ ሕብረት ማሳሰቢያ መሰረት ፣ በማሊ በህዝብ የተመረጠ መሪ ስልጣን እስከሚይዝ ድረስ የገንዘብ እርዳታ እንደማይሰጥ ማሳወቁ ይታወሳል።