የሚሸጥ አክሲዮን ያላቸውን ድርጅቶች እና ገንዘብ ያላቸውን አካላት በማገናኘት ሽያጭ እንዲከናወን የሚያግዝ ነው
ትናንት 93ኛ መደበኛ ስብሰባውን ያደረገው የሚኒስትሮች ምክር ቤት በዋና አጀንዳነት ከተወያየባቸው ሁለት አጀንዳዎች መካከል አንዱ የካፒታል ገበያ ጉዳይ ነው፡፡
በካፒታል ገበያ ላይ በቀረበለት ረቂቅ አዋጅ ላይ ተወያየው ምክር ቤቱ ያደገ እና የዳበረ የካፒታል ገበያ ለሃገር ኢኮኖሚ ዕድገትና ብልፅግና እጅግ በጣም አስፈላጊ ነው ብሏል፡፡
የካፒታል ገበያ ባደገበት ሃገር አምራች ኩባንያዎች የአክስዮን እና የብድር ሠነዶችን በመሸጥ የረዥም ጊዜ እና የአደጋ ሥጋት ያለባቸውን ነገር ግን የምርታማነት ባህሪ ያላቸው ኘሮጀክቶች በቀላሉ ፋይናንስ ማድረግ ይችላሉ ፡፡
ለህብረተሰቡ አማራጭ የቁጠባ መንገዶችን በማቅረብ ረገድም ቢሆን የካፒታል ገበያ ጠቃሚ ነው፡፡ የኢኮኖሚውን የፋይናንስ ቁጠባ ከፍ ያደርገዋል፡፡ ይህም ኢንቨስትመንትን በሃገር ውስጥ ቁጠባ ፋይናንስ እንዲሆን በማድረግ በውጭ ፋይናንስ የሚኖርን ጥገኝነት ይቀንሳል እንደ ምክር ቤቱ መግለጫ፡፡
በዚህ ረገድ ገበያው የሃገሪቱን የክፍያ ሚዛን በማስተካከል ለማክሮ ኢኮኖሚ መረጋጋት ከፍተኛ አስተዋፅኦ ያደርጋል፡፡
ምክር ቤቱም እነዚህንና ሌሎች የካፒታል ገበያ ጥቅሞችን ታሳቢ አድርጎ በብሄራዊ ባንክ ተዘጋጅቶ በቀረበለት ረቂቅ አዋጅ ላይ ነው የተወያየው፡፡
በዝርዝር ከተወያየም በኋላ አንዳንድ ማስተካከያዎችን በማከል ይጸድቅ ዘንድ ለህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት እንዲመራ ወስኗል፡፡
ለመሆኑ ይህ ዘርፈ ብዙ ጥቅሞች አሉት የተባለለት የካፒታል ገበያ ምንድነው? ምን የተለያዩ የአተገባበር ባህሪያት እና መልኮችስ አሉት? በምጣኔ ሃብት ባለሙያዎችስ ዘንድ ሊታይ የሚችልበት ሙያዊ አጽናፍ አለ?
በምጣኔ ሃብታዊ ትንታኔዎቹ የሚታወቀው ዋሲሁን በላይ ገበያውን በተመለከተ ያዘጋጀውን ትንታኔ ኢትዮጵያን ኢኮኖሚስት ቪው በተሰኘው ማህበራዊ ገጹ አጋርቷል፡፡ አል ዐይን አማርኛም እርስዎ ያነቡት ዘንድ በሚከተለው መልኩ አሰናድቶታል፡፡
ካፒታል ገበያ በኢትዮጵያ ሊጀመር ነው!
ካፒታል ገበያዎች ከባንክ ቤቶች ውጪ ተጨማሪ የገንዘብ ዝውውር የሚካሄድበት ገበያ ሲሆን በቀላሉ ብራቸውን ይዘው በሚገኙ (Saving) እና ብራቸውን ስራ ላይ ባዋሉ (Investment) አካላት መካከል አገናኝ ሆኖ የሚሰራ ገበያ (ዘመናዊ ድለላ አይነት) ነው፡፡ በዚህ ገበያ ሰዎች፣ ኩባንያዎች እና መንግስት ይሳተፋሉ፡፡
፡፡ገበያዎቹ የመጀመሪያ እና ሁለተኛ የካፒታል ሽያጭ ደረጃ ሊኖራቸው ይችላል
የካፒታሉ ገበያ በአብዛኛው የ‘ስቶክ’ እና የ‘ቦንድ’ ገበያን በመያዝ ይታወቃል፡፡ በተጨማሪም የውጪ ምንዛሬ መገበያያ (currency and foreign exchange markets) ም አለበት፡፡ እነዚህ ሁለቱ ገበያዎች የመጀመሪያ እና ሁለተኛ የካፒታል ሽያጭ ደረጃ ሊኖራቸው ይችላል፡፡
ለምሳሌ፡- አንድ ባንክ ሲቋቋም የሚሸጠው አክሲዮን የመጀመሪያ ገበያ ሲሆን፣ አክሲዎን የገዙ ሰዎች አክሲዎኖቻቸውን በተለያየ ምክንያት ለሶስተኛ ወገን በሽያጭ የሚያስተላልፉበት ገበያ ደግሞ ሁለተኛ ግብይት ይባላል፡፡ በዚህ ሁኔታ ካፒታል ገበያ የሽያጭ ዝውውሮችን የማፋጠን አቅም አለው ማለት ነው፡፡
በኢትዮጵያ እስካሁን ሰዎች የገዙትን አክሲዎን ለሶስተኛ ወገን የሚሸጡበት አሰራር የለም፡፡ ነገር ግን ለራሱ አክሲዮን ለገዙት ተቋም አክሲዮኑን ሊሸጡ የሚችሉበት አሰራር ግን አለ፡፡ ተቋሙ ለሌላ የአክሲዮን ባለድርሻ በሽያጭ ሊያቀርበው የሚችልበት አሰራርም አለ፡፡ ኢትዮጵያ በቅርቡ ልትጀምር ስለማሰቧ የሰማነው ታዲያ ይህንን ገበያ ነው፡፡
አንድ ድርጅት በሁለት መንገድ አክሲዮን ሊሸጥ ይችላል፡፡
አንደኛው፡- ሲቋቋም ለተለያዩ አካላት አክሲዎኖችን ለሽያጭ በማቅረብ ካፒታል መስርቶ ድርጅት የሚከፈትበት ሲሆን ድርጅት ለመክፈት ባለድርሻዎችን (የመስራቾች) ገንዘብ መሰብሰብ እና የሚፈለገውን የገንዘብ አቅም ማሟላት አለበት፡
ለምሳሌ፡- ባንክ ቤት ለማቋቋም ‘ትንሹ እና ከፍተኛው የአክሲዎን ዋጋ ይሄ ነው! ግዙ!’ የሚል ማስታወቂያ የምንሰማው ማለት ነው፡፡ የምስረታ ሃሳቡን ያመጡ ሰዎች ከብሄራዊ ባንክ ፍቃዱን ይወስዱ እና የአንድ እጣ ዋጋ እንዲሁም ከፍተኛ እና ዝቅተኛ የእጣ ብዛትን ይወስናሉ (የአንድ እጣ ዋጋ አንድ ሺህ ብር፣ አንድ ሰው መግዛት የሚችለው ዝቅተኛ የእጣ ብዛት 10 (10ሺ ብር ማለት ነው) እንዲሁም ከፍተኛው የእጣ ብዛት 20ሺ (20 ሚለዮን ብር ማለት ነው)) ብለው ሊወስኑ ይችላሉ፡፡ በየማስታወቂያው የምትሰሙት ማለት ነው፡፡
የመጀመሪያ ገበያ (Primary Market) ይባላል ነገር ግን አንድ ግለሰብ የገዛውን ቦንድ ገበያው ተፈጥሮ ለሌላ ሰው መሸጥ ቢፈልግ ሁለተኛ ገበያ (Secondary Market) ይባላል። አሁን በሀገራችን የሌለው እና ሊፈጠር የታቀደው ይሄ ለሶስተኛ አካል መሸጥ እና መግዛትን የሚፈቅደው ገበያ ነው።
ሁለተኛው፡- ስራ የጀመሩ ድርጅቶች (የግለሰብ ድርጅት፤ በአክሲዮን የተቋቋመ ድርጅት እንዲሁም የመንግስት የልማት ድርጅት) በተለያየ ምክንያት
ለምሳሌ፡- የመስሪያ ካፒታል ለመጨመር እና ድርጅቱን ለማስፋፋት በማሰብ፤ ኪሳራን ለመጋራት በማሰብ እንዲሁም የመንግስት የልማት ተቋም ከሆነ የተወሰነ ድርሻውን ወደ ግል ለማዞር በማሰብ አክሲዎናቸውን ለገበያ ያቀርባሉ ማለት ነው፡፡ መንግስት የኢትዮ ቴሌኮምን 45 ከመቶ እሸጣለው ያለበት አሰራር ማለት ነው፡፡
ስለዚህ የካፒታል ገበያ አስፈላጊነት የሚሸጥ አክሲዮን ያላቸውን ድርጅቶች እና ገንዘብ ያላቸውን አካላት በማገናኘት ሽያጭ እንዲከናወን ማገዝ ነው፡፡ በተለይ ሰዎችም ሆኑ ድርጅቶች ቀድመው የገዟቸውን አክሲዮኖች የትርፋማነት ሁኔታ እያዩ ለ3ኛ ወገን የመሸጥ እድል እንዲኖራቸው እንዲሁም በቀላል ካፒታል ተጨማሪ የፈለጉትን ድርጅት አክሲዮን የመግዛት እድል እንዲኖራቸው ማስቻል ነው፡፡
የካፒታል ገበያ የሚመራው በኤሌክትሮኒክስ ዘዴ ነው!
በዚህ ዘመናዊ ግዜ የካፒታል ገበያ የሚመራው በኤሌክትሮኒክስ ዘዴ ነው፡፡ ማለትም ሰዎች በ‘ኦንላይን’ ለሽያጭ የቀረቡ አክሲዮኖችን እና ዋጋቸውን መረጃ ከማግኘት ተጨማሪ ይገዛሉ ይሸጣሉ፡፡ ድርጅቶችም የሚሸጥ አክሲዮን ሲኖራቸው የሚያሳውቁበት የአሰራር ዘዴ ይኖራል፡፡
ካፒታል ገበያ እንዲጀመር ፍቃድ የመስጠቱ ስልጣን የብሄራዊ ባንክ ነው፡፡ ባንኩ ገንዘብ ነክ ጉዳዮችን መቆጣጠር እና የማስተዳደር ስልጣን አለው፡፡ በቅድሚያ ገበያውን የማስተዳደሪያ ህግ እና ተቆጣጣሪ አካል ማቋቋም ዋና ስራ ነው፤ ምክንያቱም ገበያው በማን እና እንዴት ይመራ?፤ እነማን ይሳተፉ? የሚለውን መመለስ ስለሚያስፈልግ፡፡
የውጪ ባለሃብቶች እና ድርጅቶች ይሳተፋሉ ወይስ አይሳተፉም የሚለውን፣ ታክሱ እንዴት ይሁን? የሚሉ እና ሌሎች መሰል ስራዎች መሰራት አለባቸው፡፡ በብሄራዊ ባንክ ስር እራሱን የቻለ ተቋም የሚፈጠርም ይመስለኛል፡፡
ለምሳሌ፡- የውጭ ባለሃብት በሀገር ውስጥ አክሲዮን ቢሸጥ ዜጎች አክሲዮኑን የሚገዙት በብር ቢሆንም ከብሄራዊ ባንክ በሚገባው ስምምነት መሰረት ግዜውን ጠብቆ የሽያጭ ዋጋውን በውጪ ምንዛሬ መውሰዱ ስለማይቀር የውጨ ምንዛሬ ክምችትን ያሳጣል ስለዚህ አደገኛ ነው ተብሎ ይታሰባል፡፡ ይሄ ሁሉ ለመሆን ግን የምንዛሬ ሁኔታው ወደ በገበያ የሚወሰን (Floating Exchange rate) መሄድ አለበት፡፡
ይሄ ገበያ በመቋቋሙ ቀላል የሆነ የገንዘብ ዝውውር ስለሚፈጥር እና ባለሃብቶች በቀላሉ መነሻ እና ማስፋፊያ ካፒታል ስለሚያገኙ መዋዕለ ንዋይ (ኢንቨስትመንት) እንደሚስፋፋ ይታሰባል፡፡
ገበያው ሲከፈት በዘርፉ ልምድ ያላቸው አካላት ህጋዊ ድርጅት በመክፈት ድርጅቶችን በተጨማሪ አክሲዮን እንዲሸጡ፤ አዳዲስ ድርጅቶች እንዲቋቋሙ፤ ግለሰቦች አክሲዮን እንዲገዙ እና እንዲሸጡ የማማከር እና የማከናወን ስራዎችን መጀመራቸው አይቀርም፡፡
በተለይ አዲስ የተመረቁ ወጣቶች (ፋይናንስ እና IT አካባቢ ያሉ) ይህንን ዘርፍ ቢያጠኑት እና ቢሳተፉበት በርካታ የስራ እድል እና የቢዝነስ አማራጭ ለኢኮኖሚው መፍጠር ይቻላል እላለሁ፡፡ ስለዚህ መንግስት ሆይ ካፒታል ገበያ ቢዘገይም ስርዓት ተበጅቶለት በቅርቡ ቢጀመር ኢኮኖሚያችን ተጨማሪ የመነቃቂያ መንገድ ያገኛል እላለሁ፡፡