አስተራዜኒካ ኩባንያ የኮሮና ቫይረስ ክትባት የደም መርጋት በሽታ እንደሚያስከትል አመነ
ኮቪሽልድ የተሰኘው የኮሮና ቫይረስ ክትባት በ150 ሀገራት ላሉ ዜጎች በክትባት መልክ ተሰጥቷል
ክትባቱን የወሰዱ 50 ሰዎች የ100 ሚሊዮን ፓውንድ የጉዳት ካሳ እንዲከፈላቸው ክስ መስርተዋል
አስተራዜኒካ ኩባንያ የኮሮና ቫይረስ ክትባት የደም መርጋት በሽታ እንደሚያስከትል አመነ፡፡
እስከ ታህሳስ 2023 ድረስ 61 ሚሊዮን የዓለማችን ዜጎች በኮሮና ቫይረስ ምክንት ህይወታቸውን አጥተዋል፡፡
የሚሞቱ ዜጎችን ለማዳን በ150 የዓለማችን ሀገራት በክትባት መልክ ከተሰጡ ክትባቶች መካከል መቀመጫውን ለንደን ባደረገው የአስተራዜኒካ ኩባንያ ምርት የሆነው ኮቪሽልድ የተሰኘው ክትባት ዋነኛው ነው፡፡
የዚህ ኩባንያ ምርት የሆነውን ኮቪድሽልድ የተሰኘውን ክትባት ወስደን ለደም መርጋት እና በሰውነት ውስጥ ለሚከሰት የደም መፍሰስ ችግር ተዳርገናል ያሉ ዜጎች ክስ መስርተዋል፡፡
50 ይናሉ የተባሉት እነዚህ ተጎጂዎች አስተራዜኒካ የተሰኘው ኩባንያ 100 ሚሊዮን ፓውንድ የጉዳት ካሳ ሊከፍለን ይገባል ሲሉ ክስ መመስረታቸውን ዘ ቴሌግራፍ ዘግቧል፡፡
ቻይና በትንፋሽ የሚወሰድ የኮሮና ቫይረስ መከላከያ ክትባት ይፋ አደረገች
ክስ የተመሰረተበት አስተራዜኒካ ኩባያም ኮቪሽድ የተሰኘው የኮሮና ቫይረስ ክትባት የደም መርጋትን ጨምሮ ሌሎች የጎንዮሽ ጉዳቶች እንዲከሰት ምክንያት እንደሚሆን አውቃለሁ ብሏል፡፡
ተጎጂዎች ባቀረቡት ክስ ላይ ክትባቱን በመውሰዳቸው ምክንያት ከስራ መቅረትን ጨምሮ በየዕለቱ የተለመዱ ስራዎችን መከወን እንደተሳናቸው ተናግረዋልም ተብሏል፡፡
የዓለም ጤና ድርጅት በበኩሉ አስተራ ዜኒካ ኩባንያ ያመረታቸው የኮሮና ቫይረስ ክትባቶች ካደረሱት ጉዳት ይልቅ ያተረፉት የሰው ህይወት ይበልጣል ሲል ምላሽ ሰጥቷል፡፡
ድርጅቱ አክሎም ኮቪድሽልድ ክትባት በእንግሊዝ እና በህንድ በብዛት እንዲመረቱ ተደርጎ ወደ 150 የዓለማችን ሀገራት መሰራጨታቸው የብዙዎችን ህይወት መታደግ አስችሏልም ብሏል፡፡
ይሁንና ክትባቱን በወሰዱ የተወሰኑ ሰዎች ላይ የደም መርጋት እና መሰል የጤና እክሎችን አድርሷል ሲልም የዓለም ጤና ድርጅት ተናግሯል፡፡