በአውሮፓ የጥገኝነት ጠያቂዎች ቁጥር ከ2015/16 ወዲህ ከፍተኛ ደረጃ ደረሰ
የእስራኤል እና ሀማስ ጦርነት መቀስቀሱን ተከትሎ ደግሞ የጥገኝነት ጥያቄ የሚያቀርቡ ፍለስጤማውያን ቁጥር 11ሺ ገደማ በመድረስ አዲስ ሪከርድ ሆኗል
የአውሮፓ ህብረት በ2015/16 ከተከሰተው ቀውስ ወዲህ ስደተኞች በዚያው እንዲቆዩ ከመካከለኛው ምስራቅ እና ከሰሜን አፍሪካ ሀገራት ጋር ስምምነት አድርጎ ነበር
በአውሮፓ የጥገኝነት ጠያቂዎች ቁጥር ከ2015/16 ወዲህ ከፍተኛ ደረጃ ደርሷል ተባለ።
በአውሮፓ ህብረት በፈረንጆቹ 2023 የጥገኝነት ጠያቂዎች ቁጥር በ18 በመቶ በማደግ 1.14 ሚሊዮን መድረሱን እና ይህም ከ2015/16 የስደተኞች ቀውስ ወዲህ ከፍተኛ ቁጥር መሆኑን ከ'ዩሮፒያን ዩኒየን ኤጀንሲ ፎር አሳይለም' የተገኘው መረጃ ያመለክታል።
ይህ መረጃ በአውሮፓ ከሚካሄዱት ምርጫዎች በፊት ስለስደተኞች እና ስለቀኝ ዘመምነት የሚደረጉ ክርክሮችን ሊያቀጣጥለው ይችላል ተብሏል። በመረጃው መሰረት ሶሪያውያን እና አፍጋኖች ከፍተኛውን የጥገኝነት አመልካቶቾ ቁጥር ይሸፍናሉ።
የጥገኝነት ጥያቄ በማመልከት ቱርኮች ሶስተኛ ደረጃ ላይ ተቀምጠዋል።
የእስራኤል እና ሀማስ ጦርነት መቀስቀሱን ተከትሎ ደግሞ የጥገኝነት ጥያቄ የሚያቀርቡ ፍለስጤማውያን ቁጥር 11ሺ ገደማ በመድረስ አዲስ ሪከርድ ሆኗል። ነገርግን አብዛኞቹ የአውሮፓ ሀገራት ለፍልስጤም የሀገርነት እውቅና ባለመስጠታቸው በትክክል መመዝገብ አስቸጋሪ መሆኑን ኤጀንሲው ጠቅሷል።
ጀርመን በአጠቃላይ በአውሮፓ ህብረት ከቀረበው የጥገኝነት ጥያቄ 1/3ኛውን በመቀበል በድጋሚ ቀዳሚ የጥገኝነት ጠያቂዎች መዳረሻ ሆናለች።
ኤጀንሲው መረጃውን ይፋ ያደረገው የ'አውሮፓ ቦርደር ፕሮቴክሽን ኤጀንሲ' ፍሮንቴክስ ህገወጥ የድንበር ማቋረጥ ከ2016 ወዲህ ከፍ ማለቱን ከመዘገበ ከአንድ ወር በኋላ ነው።
የጥገኝነት ጠያቂዎች ቁጥር እና የህገወጥ የድንበር ማቋረጥ ክስተቶች መጨመር፣ ስደትን እንዴት እንግታ የሚሉ ውይይቶችን የሚያጠናክሩ ሆነዋል።
የአውሮፓ ህብረት በ2016 ከተከሰተው ቀውስ ወዲህ የድንበር ቁጥጥሩን እና የጥገኝነት ህጎችን ከማጥበቅ ባሻገር ስደተኞቾ በዚያው እንዲቆዩ ከመካከለኛው ምስራቅ እና ከሰሜን አፍሪካ ሀገራት ጋር ስምምነት አድርጎ ነበር።