ፖለቲካ
ቱኒዚያ የአውሮፓ ህብረት ለስደተኞች ቀውስ የመደበውን የገንዘብ እርዳታ ውድቅ አደረገች
ሁለቱ ወገኖች ከሰሜን አፍሪካዊቷ ሀገር ወደ አውሮፓ እየጨመረ የመጣውን ስደት ለመቀነስ ተስማምተዋል
ፕሬዝዳንት ሰይድ የአውሮፓ ህብረት ስምምነቱን አላከበረም ብለዋል
የቱኒዚያ ፕሬዝዳንት ኬሲ ሰይድ በአውሮፓ ህብረት ይፋ የሆነውን የገንዘብ እርዳታ ውድቅ አድርገዋል።
ፕሬዝዳንቱ የገንዘቡ መጠን አነስተኛና ከሦስት ወር በፊት ከተደረሰው ስምምነት ያፈነገጠ ነው ብለዋል።
የፕሬዝዳንት ሰይድ እርምጃ የሁለቱ ወገኖችን ስልታዊ አጋርነት ሊጎዳው ይችላል ተብሏል።
ሁለቱ ወገኖች በሀምሌ ወር ህገ-ወጥ የሰዎች ዝውውርንና የድንበር ጥበቃን ጠበቅ ለማድረግ የተስማሙ ሲሆን፤ ከሰሜን አፍሪካዊቷ ሀገር ወደ አውሮፓ እየጨመረ የመጣውን ስደት ለመቀነስ የተለመ ነው።
የአውሮፓ ኮሚሽን ከአፍሪካ የሚነሳውን ህገ-ወጥ የሰዎች ዝውውር ለመግታት ለቱኒዚያ 127 ሚሊዮን ዩሮ ለመልቀቅ ውሳኔ አሳልፏል።
የሀምሌው ስምምነት የተጎዳውን የሀገሪቱን ምጣኔ-ሀብት ለመጠገንና የስደት ቀውስን መላ ለማለት አንድ ቢሊዮን ዩሮ እርዳታ ቱኒዚያ እንደምታገኝ ይጠቅሳል።
ፕሬዝዳንት ሰይድ ይህ ስምምነትና በኮሚሽኑ ይፋ የሆነው ገንዘብ በመለያየታቸው ውድቅ እንዳደረጉት ገልጸዋል።
የኮሚሽኑ ገንዘብ ይፋ የሆነው ከ10 ቀናት በኋላ መሆኑን የጠቀሰው ሮይተርስ፤ የቱኒዚያ ባለስልጣናት ደስተኛ አለመሆናቸውን ዘግቧል።