ብሪታንያ የስደተኛ ሰራተኞችን ቁጥር በ300 ሺህ የሚቀንስ ውሳኔ አሳለፈች
ሀገሪቱ ቀጣሪዎች ለባለሙያዎች የሚከፍሉት ዝቅተኛ ደመወዝ ወደ 50 ሺህ ዶላር እንዲያድግ ወስናለች
ከፍተኛ የሰው ሃይል የሚፈልጉ ኩባንያዎች ግን ውሳኔውን እየተቃወሙት ነው
ብሪታንያ በየአመቱ እየጨመረ የመጣውን የስድተኞች ቁጥር ለመቀነስ ያስችላል ያለችውን ውሳኔ አሳልፋለች።
ባለፈው ወር የወጣ መረጃ በ2022 745 ሺህ ሰዎች ህጋዊ መንገድን ተከትለው ወደ ሀገሪቱ መግባታቸውን ያመለክታል።
ከህንድ፣ ናይጀሪያ እና ቻይና ወደ ብሪታንያ የሚገቡ ሰራተኞች ቁጥርም እያሻቀበ መሆኑ ተገልጿል።
ስደተኞችን ወደ ሩዋንዳ ለመመለስ ውጥን የያዘው የሪሺ ሱናክ አስተዳደር በህጋዊ መንገድ ወደ ብሪታንያ የሚገቡ ሰዎችን ቁጥር ለመቀነስ አዲስ ውሳኔ አሳልፏል።
ቀጣሪ ድርጅቶች ለባለሙያዎች የሚከፍሉት ዝቅተኛ ደመወዝ ከ26 ሺህ ፓውንድ ወደ 38 ሺህ 700 ፓውንድ (48 ሺህ 900 ዶላር) እንዲያድግ ተወስኗል።
ይህም በገፍ እየገቡ የሚገኙ ሰራተኞችን ቁጥር እንደሚቀንስ ታምኖበታል።
የብሪታንያ የሀገር ውስጥ ጉዳይ ሚኒስትር ጀምስ ክሌቨርሊ እንደሚሉት ውሳኔው በየአመቱ ወደ ሀገሪቱ የሚገቡ ሰዎችን ቁጥር በ300 ሺህ ዝቅ ያደርጋል።
የጤና ባለሙያዎች ቤተሰቦቻቸውን ወደ ብሪታንያ የሚያስገቡበት የቪዛ ስርአት ጥብቅ እንዲሆንና ክፍያውም እንዲጨምር ተወስኗል።
ይህም የጤና ባለሙያዎች ከቤተሰቦቻቸው ከምትነጥላቸው ብሪታንያ ይልቅ ሌሎች ሀገራትን እንዲያማትሩ በማድረግ ከፍተኛ የሰው ሃይል ክፍተት ይፈጥራል የሚል ተቃውሞ እየቀረበበት ነው።
ጥናቶችም በብሪታንያ ተቀጥረው የሚሰሩ የውጭ ሀገር ሰራተኞች ቁጥር በጣም ዝቅተኛ መሆናቸውንና በተለያዩ ዘርፎች አሁንም ሰፊ የሰራተኛ ክፍተት እንዳለ ያሳያሉ።
የሪሺ ሱናክ አስተዳደር ያሳለፈው ውሳኔም ባንኮችን ጨምሮ የሰለጠነ የሰው ሃይል የሚፈልጉ ተቋማትን ለችግር እንደሚዳርግ የንግድ ተቋማት ማህበራት እየገለጹ መሆኑን ሬውተርስ ዘግቧል።