በኢራን ቢያንስ 100 ተቃዋሚዎች የሞት ቅጣት እንደሚጠብቃቸው ተገለጸ
የታሳሪዎቹ ቤተሰቦች ምንም ነገር ትንፍሽ እንዳይሉ ማስፈራሪያና ዛቻ እየደረሰባቸው ነውም ተብሏል
በኢራን እስካሁን 476 ተቃዋሚዎች መገደላቸው የመብቶች ተሟጋች ድርጅት መረጃ ያመለክታል
በኢራን ቢያንስ 100 ተቃዋሚዎች የሞት ቅጣት እንደሚጠብቃቸው አንድ የመብት ተሟጋች ድርጅት ገለጸ።
መቀመጫውን ኖርዌይ ያደረገው የኢራን ሰብዓዊ መብቶች ተሟጋች ድርጅት (IHR) በዚህ ሳምንት እንዳስታወቀው - ታዳጊ ወንዶች እና ሁለት የ22 አመት ሴቶችን ጨምሮ - 100 ተቃዋሚዎች በመላ ሀገሪቱ በተቀሰቀሰው ሰልፎች ላይ ተሳትፈዋል በሚል ሞት ተፈረዶባቸው አደጋ ላይ ናቸው።
አሃዙ ከዚህም ሊበልጥ ይችላል ያለው ድርጅቱ፤ የታሳሪዎቹ ቤተሰቦች ምንም ነገር ትንፍሽ እንዳይሉ ማስፈራሪያና ዛቻ እየደረሰባቸው መሆኑም ተገልጿል፡፡
በተቃውሞ ሰልፍ ላይ ተሳትፈዋል በሚል የሞት ፍርድ ከተፈረደባቸው ውስጥ ሁለት ሰዎች መገደላቸውንም ጭምር አስታውቋል፡፡
"በጸጥታ ኃይሎች የተገደሉት ግለሰቦች ሞህሰን ሸካሪ እና ማጂድሬዛ ሪሃንቫርድ የተባሉ ሁለት የ23 ዓመት ኢራናውያን ሲሆኑ ጥፋታቸውም የአምላክን ክብር አሳንሰዋል በሚል ነው” ተብሏል፡፡
በዚህ የተደናገጠው የሀገሪቱ መንግስትም ሁከት ፈጣሪዎች ናቸው ባላቸው በመቶዎች በሚቆጠሩ ሰዎች ላይ ክስ መመስረቱ የሀገሪቱ ዓቃቤ ህግ ማስታወቁ አይዘነጋም፡፡
“ሁከት ፈጣሪዎች” ላይ ፈጣን ፍርድ ለመስጠት ቃል መግባቱም እንዲሁ ይታወሳል፡፡
ኪዘህም በተጨማሪ የጸጥታ ኃይሎች በወሰዱት እርምጃ እስካሁን 64 ልጆችና 34 ሴቶች የሚገኙባቸው 476 ሰዎች መገደላቸው የኢራን ሰብዓዊ መብቶች ተሟጋች ድርጅት መረጃ ያመለክታል፡፡
የ22 ዓመቷ ኢራናዊት ኩርድ ማህሳ ጸጉርሽን በትክክል አልሸፈንሽም በሚል በቴህራን የደንብ አስከባሪ ፖሊሶች በቁጥጥር ስር ከዋለች ከሶስት ቀናት በኋላ በእስር ላይ እያለች ህይወቷ ማለፉ የሚታወስ ነው።
የማህሳ አሚኒ ሞት ታዲያ በኢራን የተቃውሞ ማዕበል የቀሰቀሰ ሲሆን በኢራን ውስጥ ፈላጭ ቆራጭ ተደረገው የሚታዩት አያቶላ አሊ ካሜኒ እንደዚህ አይነት ተቃውሞ ሲገጥማቸው በኢራን ታሪክ ውስጥ የመጀመሪያው ነው ተብሏል፡፡