እስራኤል የኢራንን የኒዩክሌር ጣቢያዎች “አደባያለሁ” አለች
የሀገሪቱ መከላከያ ሚኒስትር ቤኒ ጋንዝ እንዳስታወቁት፥ ጥቃቱ በሁለት ወይም በሶስት አመት ውስጥ ሊፈጸም ይችላል
ቴህራንና ቴል አቪቭ በኒዩክሌር እና ሌሎች ቀጠናዊ ጉዳዮች እንደ ጠላት የሚተያዩ ሀገራት ናቸው
እስራኤል የኢራንን የኒዩክሌር ጣቢያዎች ልታደባይ እንደምትችል አስታወቀች።
በቀጣይ ሁለት ወይም ሶስት አመት ውስጥ ጥቃቱ ሊፈጸም እንደሚችልም ነው የሀገሪቱ መከላከያ ሚኒስትር ቤኒ ጋንዝ ያስታወቁት።
እስራኤል ጥቃት ልትፈጽም ያቀደችበትን ጊዜ ይፋ ስታደርግም ይህ የመጀመሪያው ነው ተብሏል።
የኢራኑን የ2015 የኒዩክሌር ስምምነት ዳግም ወደ ስራ ለማስገባት የሚደረገው አለም ጥረት በተቋረጠበት ሁኔታ ቴህራን የዩራኒየም ማበልጸግ ስራዋን ገፍታበታለች።
የኒዩክሌር አረር ለማምረት ግን አመታት ይወስድባታል ቢባልም የእስራኤል ባለሙያዎች እርምጃ እንዲወሰድባት ሲወተውቱ ይደመጣል።
ቴል አቪቭ ግን ከዛቻ ያለፈ እርምጃን መውሰድ አልቻለችም።
የመከላከያ ሚኒስትሩ ቤኒ ጋንዝ ባልተለመደ መልኩ ጊዜ ጠቅሰው የኢራንን የኒዩክሌር ጣቢያዎች እናደባያለን ማለታቸውም ከማስጠንቀቂያ አያልፍም የሚሉ ተንታኞች አሉ።
በተለይ ሀገራቱ ከላቸው ርቀትና ኢራን ከገነባችው የመከላከያ አቅም አንጻር የቤኒ ጋንዝ ዛቻ ብዙም የሚያስደነግጥ አይደለም ባይ ናቸው።
የእስራኤል የወታደራዊ ጉዳዮች የስለላ ተቋም የቅርብ ሪፖርት እንደሚያመላክተው ኢራን በ2023 የኒዩክሌር ፕሮግራሟን ታፋጥናለች ተብሎ አይጠበቅም።
ቴህራን ተጨማሪ ከባድ ማዕቀቦች ከተጣሉበት ግን ሁኔታዎች ሊቀየሩ እንደሚችሉም ሪፖርቱ ማመላከቱን ሬውተርስ አስነብቧል።
ኢራንን በኒዩክሌር እና ሌሎች ቀጠናዊ ጉዳዮች እንደ ጠላት የምትመለከታት እስራኤል የኒዩክሌር የጦር መሳሪያ እንዳላት አላረጋገጠችም፤ የለኝም ብላም አላስተባበለችም።
ይሁን እንጂ የመጀመሪያውን የኒዩክሌር ቦምብ በ1966 ያገኘችው ሀገር ከኒዩክሌር ባለቤት ሀገራት የሚመድቧት በርካታ ናቸው።
ቴል አቪቭ በ1970 የተፈረመውን የኒዩክሌር ሃይል ባለቤት ለመሆን የሚደረግ እሽቅድምድም የሚገታ ስምምነት አለመፈረሟም ከተጠያቂነት ለመደበቅ ረድቷታል ነው የተባለው።
በቀጠናዊ ጉዳዮች እርስ በርስ እንደ ጠላት የሚተያዩት ሀገራት ከቃላት የተሻገረ ጦርነት ውስጥ ይገባሉ ተብሎ አይጠበቅም።