ኢራን በደቡባዊ ውሀ የአሜሪካ ጦር ኃይል መጨመሩ ተቀባይነት የለውም አለች
ሀገሪቱ በቀጣናው ሰላምና መረጋጋትን ለማጠናከር በባህር ዳርቻዎች እና በቀጣናው ሀገራት ትብብርን ማጠናከር ነው ብላለች
ኢራን አሜሪካ ለዓመታት በቀጠናው ውስጥ የማተራመስ ሚና በመጫወት መረጋጋት እና ደህንነትን አላመጣችም በማለት ከሳለች
የኢራን ውጭ ጉዳይ ሚንስቴር ቃል አቀባይ ናስር ካናኒ በሀገሪቱ ደቡባዊ ውሀ የአሜሪካ ጦር ኃይል መጨመሩ ተቀባይነት የለውም ብለዋል።
ቃል አቀባዩ የአሜሪካ ጦር በደቡባዊው የሀገሪቱ ዓለም አቀፍ ውሃ ላይ እንቅስቃሴ ለመጨመር ማንኛውም እቅድ በአካባቢው መረጋጋት እና ሰላምን አደጋ ላይ የሚጥል በመሆኑ ተቀባይነት የለውም ብለዋል።
"በቀጣናው በተለይም በዓለም አቀፍ የውሃ አካላት ውስጥ ሰላምና መረጋጋትን ለማጠናከር ጥሩ መንገድ በባህር ዳርቻዎች እና በቀጣናው ሀገራት መካከል ያለውን ትብብር ማጠናከር ነው ብለን እናምናለን" ሲሉ ለትብብር ጥሪ አቅርበዋል።
ናስር ካናኒ እንደ አለመታደል ሆኖ አሜሪካ ለዓመታት በቀጠናው ውስጥ ገንቢ ያልሆነ እና የማተራመስ ሚና በመጫወት መረጋጋት እና ደህንነት አላመጣችም ብለዋል።
የአሜሪካ መንግስት ሰበቦችን በመጠቀም በአካባቢው ዓለም አቀፍ ውሃ ውስጥ የሚደረጉ ወታደራዊ እርምጃዎችን የማጠናከር እና የማተራመስ ጥረት አድርጓል ሲሉም ከሰዋል።
በቅርቡ የእስራኤል ንብረት በሆነው የነዳጅ ጫኝ መርከብ ላይ ስለደረሰው ጥቃት የተጠየቁት ካናኒ፤ ስለ ጉዳዩ ምንም አይነት መረጃ እንደሌላቸው መናገራቸውን ሲጂቲኤን ዘግቧል።
አንድ ሰው አልባ አውሮፕላን የላይቤሪያ ባንዲራ ባለበት እና የእስራኤል ንብረት በሆነው የነዳጅ ጫኝ መርከብ በኦማን የባህር ዳርቻ ባለፈው ሳምንት ጥቃት ተሰንዝሮባታል።