“የጉባውን ጥቃት የፈጸመውን ቡድን ለመደምሰስ ጥረት እየተደረገ ነው”-የቤንሻንጉል ፖሊስ ኮሚሽን
ቡድኑ ከ2 ሳምንት በፊት በጉባ 13 ሰዎችን መግደሉ የሚታወስ ነው
የቡድኑ አካል ናቸው ተባሉ 121 ተጠርጣሪዎችና የተለያዩ የጦር መሳሪያዎች በቁጥጥር ስር ውለዋል
የጉባውን ጥቃት የፈጸመውን ቡድን ለመደምሰስ ጥረት እየተደረገ ነው
ጦር መሳሪያ ታጥቆ የሚንቀሳቀሰውንና በቤንሻንጉል ጉሙዝ ክልል መተከል ዞን ጉባ ወረዳ ጥቃት የፈጸመውን ቡድን ለመደምሰስ ጥረት እየተደረገ መሆኑን የክልሉ ፖሊስ ኮሚሽን አስታወቀ፡፡
ለዚህም የክልሉ የጸጥታ ኃይል ከሀገር መከላከያና የፌዴራል ፖሊስ ጋር በቅንጅት እየሰራ ነው ያለው ኮሚሽኑ ጫካን ተገን በማድረግ የሚንቀሳቀሰው ቡድን አካል የሆኑ 121 ተጠርጣሪዎች መያዛቸውን ገልጿል፡፡
ቡድኑ የብሔር ግጭት ለመፍጠር፣ አካባቢው የሕዳሴ ግድብ መገኛ መሆኑን ተከትሎ አለመረጋጋት እንዲፈጠር በዚህ ምክንያትም እንደ ክልል ብሎም እንደ ሀገር ትልቅ ጥፋት የመፍጠር ዓላማ ያለው ስለመሆኑም ኮሚሽነር መሀመድ ሀምደኒል ለክልሉ ኮሙኒኬሽን ቢሮ ተናግረዋል፡፡
“በተለይም አሁን ሀገር እየመራ ያለው ፓርቲም ሆነ ለውጡ እኛን አይወክለንም” በማለት ወጣቱንና ሕዝቡን ለአመጽ የሚቀሰቅሰው ቡድኑ በክልሉ ከሚገኙ ተፎካካሪ ፓርቲዎች ጋር ትልቅ የጥፋት ቅንጅትና ተገቢ ድጋፍ እንደሚያገኝም ነው ኮሚሽነር መሀመድ የተናገሩት፡፡
ኮሚሽነሩ አክለውም ወጣቶችን በመመልመል፣ በተለያዩ ምክንያቶች ከሀገር መከላከያ እና ከመንግስት የጸጥታ ሥራ የተቀነሱ ግለሰቦችን በመያዝ በሱዳን ድንበር አካባቢ አቡልታ በተባለ ቦታ በአማርኛ፣ በጉሙዝኛ እና በአረብኛ ቋንቋዎች የጥፋት ስልጠና ሲሰጥ እንደነበር በኦፕሬሽኑ ወቅት መረጋገጡንና አስረጂ መረጃዎች መገኘታቸውንም አብራርተዋል፡፡
በተለይም በለውጥ ላይ በምትገኘው የሀገሪቱ አሁናዊ ሁኔታ ላይ ያኮረፈው ያሉት ህወሓት “በአካባቢው በኢንቨስትመንት ስም የሚገኙ ባለሃብቶችን በመጠቀም ቡድኑ ለያዘው የጥፋት ተልዕኮ መሳካት የተለያዩ ድጋፎችን ሲያደርግ ነበር”ም ብለዋል ኮሚሽነሩ፡፡
በቡድኑ ላይ በተደረገ ኦፕሬሽን በቀጥታ የተኩስ ልውውጥ ሲያደርጉ በነሩበት ወቅት የተያዙትን 61 ግለሰቦች ጨምሮ፣ የሎጅስቲክስ፣ የምግብና ሌሎች ድጋፎችን ሲያደርጉ የነበሩ እና በመንግስት ኃላፊነት ላይ የነበሩ ነገር ግን ኃላፊነታቸውን በአግባቡ ያልተወጡ በድምሩ 121 ሰዎች በቁጥጥር ስር ውለው የማጣራት ሥራው ተጠናክሮ መቀጠሉን ገልጸዋል፡፡
ቡድኑ ለተለያዩ ተልዕኮ ማስፈጸሚያነት ሲጠቀምባቸው ነበሩ 6 የሞተር ሳይክሎችን ጨምሮ 1 አር ቢ ጂ የተባለ የቡድን የጦር ማሳሪያ ከ3 አቀጣጣይ እና 1 ቅምቡላ ጋር፣ 6 ክላሽ፣ 17 ኋላቀር የጦር መሳሪያዎች እንዲሁም 293 የብሬን እና 30 የክላሽ በድምሩ 223 የጥይት ፍሬዎችም በቁጥጥር ስር ውለዋል፡፡
በጦር መሳሪያ በመታገዝ ሐምሌ 20 ቀን 2012 ዓ.ም ምሽት 2፡30 አካባቢ በጉባ ወረዳ ጃዲያ ቀበሌ በተፈጸመው ጥቃት የ13 ሰዎች ሕይወት ማለፉ የሚታወስ ነው፡፡