በሀገሪቱ ምዕራባዊ ግዛቶች ከ100 በላይ ቦታዎች ላይ የሰደድ እሳት ተነስቷል
በአሜሪካ እየተባባሰ በመጣው የሰደድ እሳት በትንሹ 15 ሰዎች መሞታቸው ተገለጸ
በተለያዩ አቅጣጫዎች እየተዛመተ በሚገኘው የሰደድ እሳት ፈተና በሆነባት በሰሜን ካሊፎርኒያ ሀሙስ ዕለት 7 አስከሬን መገኘቱን ባለስልጣናት አስታውቀዋል፡፡ በዚህም በግዛቲቱ በእሳቱ ህይወታቸው ያለፈ ሰዎች ቁጥር 10 ደርሷል፡፡
በዋሺንግተን እና በኦሪጎን ግዛቶች ከቁጥጥር ዉጭ በሆነው ሰደድ እሳት ደግሞ በዚህ ሳምንት በትንሹ 5 ሰዎች መሞታቸውን ሲኤንኤን ዘግቧል፡፡
በምዕራብ አሜሪካ በሚገኙ 12 ግዛቶች በፍጥነት እየተዛመቱ በሚገኙት ከ100 በላይ የሰደድ እሳቶች ሳቢያ በርካታ ሰዎች በመፈናቀል ላይ ሲሆኑ በኦሪጎን ግዛት ብቻ ከግማሽ ሚሊዮን በላይ ሰዎች ከቤት ንብረታቸው መሰደዳቸውን የሀገሪቱ ባለስልጣናት ገልጸዋል፡፡
ሀሙስ ዕለት በኦሪጎን የሰደድ እሳቱ ያፈናቀላቸው ግማሽ ሚሊዮን ዜጎች ቁጥር ከግዛቱ ነዋሪዎች 10 በመቶ መሆኑን የኦሪጎን የአስቸኳይ ጊዜ አስተዳደር ቢሮ ይፋ አድርጓል፡፡ የተፈናቃዮች ቁጥር እየጨመረ እንደሆነም እንዲሁ፡፡
እሳቱ በተነሳባቸው አካባቢዎች ከተሞችን ጭምር ከፍተኛ ጭስ መሸፈኑም በዘገባው ተጠቁሟል፡፡
ከመላው አሜሪካ የእሳት አደጋ ሰራተኞች እሳቱን ለመቆጣጠር ጥረት በማድረግ ላይ ናቸው፡፡ ሰደድ እሳቱ እስካሁን ከ1.6 ሚሊዮን ሔክታር በላይ የሚሆን ስፍራ አቃጥሏል፡፡