በአደጋው እስካሁን 6 ሰዎች ሲሞቱ ከ175 ሺ በላይ ሰዎች ተፈናቅለዋል
የካሊፎርኒያ ሰደድ እሳት እስካሁን 400 ሺ ሄክታር ቦታ አቃጥሏል
እስካሁን 400 ሺ ሄክታር የሚሆን ቦታን ያወደመው የካሊፎርኒያ የሰደድ እሳት አሁንም እንደቀጠለ ነው፡፡
ከ 14,000 በላይ የእሳት አደጋ ተከላካዮች እሳቱን ለማጥፋት በመረባረብ ላይ ናቸው፡፡ ይሁንና በከፍተኛ መጠን ሊጨምር እንደሚችል የተተነበየው በአካባቢው ያለው ንፋስ እሳቱን ሰዎች ወደ ሚበዙባቸው አካባቢዎች ሊያዛምተው እንደሚችል ተሰግቷል፡፡
እስካሁን በእሳቱ 6 ሰዎች መሞታቸው የተረጋገጠ ሲሆን ከ175 ሺ በላይ ሰዎች ደግሞ ተፈናቅለዋል፡፡ በጥቂቱ የእሳት አደጋ ሰራተኞችን ጨምሮ 43 ሰዎች ጉዳት ደርሶባቸዋል፡፡ እስከ ትናንትናው ዕለት 115 ቤቶችም ተቃጥለዋል፡፡ በሳን ሆሴ አካባቢ የሚገኙ ተጨማሪ በሺዎች የሚቆጠሩ ሰዎችም ቤታቸውን እና አካባቢያቸውን ጥለው እንዲወጡ ማስጠንቀቂያ ተሰጥቷቸዋል፡፡
እሳቱ በአብዛኛው የደን ሽፋንን የጎዳ ሲሆን ከ2,000 ዓመታት በላይ ዕድሜ ያላቸው ዛፎች በብዛት ወድመዋል፡፡ ዛፎቹ ቁመታቸው እስከ 100 ሜትር የሚደርስ ነው፡፡ ታሪካዊው የቢግ ቤዚን ፓርክም ወድሟል፡፡
የሰደድ እሳቱ ትልቅ አደጋ መሆኑን የገለጹት የአሜሪካ ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ ወደ ካሊፎርኒያ የፌደራል መንግስት ድጋፍ መላካቸውን ቢቢሲ ዘግቧል፡፡
የካሊፎርኒያ አስተዳደር በሰደድ እሳት ተደጋጋሚ ታሪክ ካላት አውስትራሊያ በትናንትናው ዕለት ድጋፍ ጠይቋል፡፡
ሰደድ እሳት ተጨማሪ ፈተና የደቀነባት ከ650 ሺ በላይ የኮሮና ቫይረስ ታማሚዎች የተገኙባት ካሊፎርኒያ በቫይረሱ ተጠቂዎች ቁጥርም በአሜሪካ ቀዳሚ ነች፡፡