ሊጠናቀቅ በተቃረበው 2021፤ በመላው ዓለም 24 ጋዜጠኞች ተገድለዋል ተባለ
በዚሁ ዓመት በአጠቃላይ 293 ጋዜጠኞች በሙያቸው ምክንያት መታሰራቸው ተገልጿል
ከዓለማችን ቻይና ብዙ ጋዜጠኞችን ስታስር ከአፍሪካ ደግሞ ግብጽ ቀዳሚ ሆናለች
ሊጠናቀቅ በተቃረበው የፈረንጆቹ ዓመት 2021፤ በመላው ዓለም 24 ጋዜጠኞች መገደላቸው ተገለጸ፡፡
ዓለም አቀፉ የጋዜጠኞች ተቆርቋሪ ተቋም (CPJ) ባወጣው ዓመታዊ ሪፖርት በ2021 24 ጋዜጠኞች ሲገደሉ 293 ደግሞ ታስረዋል ብሏል፡፡
ይህም በታሪክ ብዙ ጋዜጠኞች የታሰሩበት ዓመት መሆኑን ነው የሲፒጄ ሪፖርት ያመለከተው፡፡
ቻይና 50 ጋዜጠኞችን በማሰር ቀዳሚ ስትሆን ምያንማር 26 እንዲሁም ግብጽ 25 ጋዜጠኞችን በማሰር ቀዳሚ የዓለማችን አገራት ናቸው፡፡
ስራ ላይ ይዋል የተባለው አዲሱ የሚዲያ ፖሊሲ ምን አዲስ ነገር ይዟል?
መንግስታት መረጃን በማፈን ተጠምደዋል ያሉት የሲፒጄ ዋና ዳይሬክተር ጆኤል ሲሞን ዓለማችን ከመቼውም ጊዜ በላይ የሚዲያ ነጻነት ችግር ውስጥ መሆኗንም ተናግረዋል፡፡
ባለፈው ዓመት በሙያቸው ምክንያት ለእስር የተዳረጉ ጋዜጠኞች ብዛት 280 የነበሩ ሲሆን ዘንድሮ ቁጥሩ በ13 ጨምሯል፡፡
ቬትናም፣ ቤላሩስ፣ ሳዉዲ አረቢያ፣ ኢራን፣ ቱርክ፣ ሩሲያ፣ ኢትዮጵያ እና ኤርትራ በአንጻራዊነት ብዙ ጋዜጠኞችን በሙያቸው ምክንያት ያሰሩ አገራት ናቸው፡፡
በአፍጋኒስታን፣ በሜክሲኮ እና በምያንማር ጋዜጠኞች በዘገባ ላይ እያሉ በጸጥታ ሃይሎች ተገድለው ህይወታቸው እንዳለፈ ተቋሙ በሪፖርቱ ገልጿል፡፡
ሲፒጄ ከ40 ዓመት በፊት ዋና መቀመጫውን አሜሪካ በማድረግ የጋዜጠኞችን ደህንነት ለማስከበር የተቋቋመ የሙያ ተቋም ነው፡፡