ስራ ላይ ይዋል የተባለው አዲሱ የሚዲያ ፖሊሲ ምን አዲስ ነገር ይዟል?
“ባለስልጣኑ እርምጃ ለመውሰድ ‘ዘገየ’ የሚሉ አሉ፡፡ ግን ልክ መቼ ነበር የነበረው? የሚለውን በትክክል ‘እዚህ ጋ ነው’ ብሎ ሊመልስ የሚችል ደግሞ የለም”- ዋና ዳይሬክተሩ
“ከዚህ በኋላ ከውጭ የሚደጎሙ ሚዲያዎች አይኖሩም ቢኖሩም ይጠየቃሉ”-ጌታቸው ድንቁ (ዶ/ር)
“ከዚህ በኋላ ከውጭ የሚደጎሙ ሚዲያዎች አይኖሩም ቢኖሩም ይጠየቃሉ”-ጌታቸው ድንቁ (ዶ/ር)
ባሳለፍነው ነሃሴ 16 የተሰበሰበው የሚኒስትሮች ምክር ቤት ብዙዎች የዘርፉ ሙያተኞች ለኢትዮጵያ የጋዜጠኝነት ሙያ እና መገናኛ ብዙሃን ዘርፍ ጉልህ አስተዋኦ ሊያበረክት እንደሚችል የተናገሩለትን አንድን ውሳኔ አሳልፏል፡፡ ውሳኔው ቀደም ሲል ተዘጋጅቶ በሚመለከታቸው የተለያዩ አካላት ምክክሮች ሲደረጉበት የነበረው ረቂቅ የሚዲያ ፖሊሲ የተሰጡ አንዳንድ አስተያየቶች ተካተውበት በስራ ላይ ይዋል በሚል የሚፈቅድ ነበር፡፡
የዘርፉን ህልውና የሚፈታተኑትን ስር የሰደዱ ችግሮች ጨምሮ ለዘርፉ እድገት ማነቆ ሆነዋል በሚል ተደጋግመው የሚነሱ እንቅፋቶችን ለመቅረፍ እንደሚያስችል የታመነበት ፖሊሲው ምን ይዟል፣ ምንንስ ታሳቢ አድርጎ ወጣ፣ ችግሮችንስ ምን ያህል ሊያቀል ይችላል በሚል አል ዐይን አማርኛ ከኢትዮጵያ ብሮድካስት ባለስልጣን ዋና ዳይሬክተር ጌታቸው ድንቁ (ዶ/ር) ተከታዩን ቆይታ አድርጓል፡፡
አብራችሁን ዝለቁ!
አል ዐይን፦ ለቃለ መጠይቁ ፍቃደኛ ስለሆኑ እናመሰግናለን፡፡ ፖሊሲው ከአሁን ቀደም መኖር የነበረበት ነገር ግን ያልነበረ ነው፡፡ አሁን ግን መውጣት ብቻ አይደለም ስራ ላይ ይዋል ተብሏል፡፡ ይህ በመባሉ ዘርፉ ምን ሊያገኝ ይችላል? ከአሁን ቀደምስ ባለመኖሩ ምን ታጣ?
ጌታቸው ድንቁ (ዶ/ር)፦ ጥሩ እንግዲህ በኢትዮጵያ ብዙ ፖሊሲዎች አሉ፤ ብዙ ዘርፎችን የተመለከቱ፡፡ በመገናኛ ብዙሀን ዘርፍ ግን እኔ እስከማውቀው በ1994 ላይ ይመስለኛል “የዲሞክራሲ ስርዓት ግንባታ ጉዳዮች በኢትዮጵያ” የሚል አንድ መድብል ነበረ፡፡ እዛ ላይ ስለሚዲያ ዝም ብሎ እንደ “ፓሲንግ ሪማርክ” አይነት የተጠቀሰ ነገር አለ፤ እንጃ አንድ ገጽ መሙላቱን፡፡
ከዛ ደግሞ ወደ 2007 ገደማ በቀድሞው የኮሙኒኬሽን ጉዳዮች ጽ/ቤት አማካኝነት የተደረገ ጥረት ነበር፡፡ እሱም ገና በረቂቅ ደረጃ ላይ እያለ ‘ልማታዊ ምልከታን ነው የያዘው አያሰራም’ በሚል ከሚዲያዎች ተቃውሞ ገጠመውና መከነ፡፡
ከዚያ በኋላ ከተለያዩ ተቋማት ሰዎች ተውጣጥተው እኔም ከዩኒቨርሲቲ ተወክዬ የውጭ ሀገር ልምዶችን አይተን ሀገራዊ ጥናት ተጠና፡፡ በጥናቱ ፖሊሲ አለመኖሩ እንደ ክፍተት ታይቶ ነበር፡፡ ስለዚህ ያ ክፍተት ሆኖ ከተለየ ፖሊሲ እንዲኖር መሰራት ነበረበት፡፡ ያን ተከትሎም የሃገራችን ነባራዊ ሁኔታ የተለያዩ ሀገራት ተሞክሮም ተካቶበት ባለድርሻ አካላቱ የተወያዩበት ቢያንስ 6 ጊዜ ያህል የተስተካከለ የተጨመቀ 29 ገጽ ያለው ፖሊሲ ተዘጋጀ፡፡
የሚስትሮች ምክርቤትም ሲቀርብለት ያን ያህል የጎላ የሚባል ትችት አላቀረበበትም፡፡ ከጥቂት ማስተካከያዎች በስተቀር ጸድቆ በስራ ላይ እንዲውል ነው የወሰነው፡፡ በዚያ መሰረት አሁን አሳትመነው ለሚመለከታቸው እንዲሰራጭ እንሰራለን፡፡
ፖሊሲው አስቻይ፣ የዲሞክራሲ ስርዓትን ለመገንባት የሚችል ነጻ፣ ገለልተኛና ሙያዊ የሆነ ኃላፊነት የሚሰማው ሚዲያ እንዲፈጠር የሚያስችል ነው፡፡ ከዛ ውጭ ምንም ዓይነት የአይዲዮሎጂ/ርዕዮተ ዓለም ቅኝት ያለበት አይደለም፡፡
አል ዐይን፦ እርስዎ ጥቂት ያሏቸው ምክር ቤቱ ግን ተስተካክለው ስራ ላይ ይዋሉ ያላቸው አስተያየቶች ምንድን ነበሩ?
ጌታቸው ድንቁ (ዶ/ር)፦ በጣም ጥቂት ናቸው የተሰጡት አስተያየቶች፡፡ ለምሳሌ ራዕይ በሚቀመጥበት ጊዜ ዓ.ም. ተቀምጦ እስከ 2017 ድረስ የሚል አለ፡፡ ፖሊሲ ስለሆነ፣ ዓመተ ምህረትን ማስቀመጥ ተገቢ ነው ወይ የሚል ተገቢ ጥያቄ ተነስቷል፡፡ ሌሎችም እንደዚህ የመሳሰሉ ጥቃቅን ነገሮች ተነስተዋል፡፡
ይሄ ቢወጣ ፣ ይሄ ቢገባ የሚል እንጂ ፤ ትልቅ የሚባል የሀሳብ ልዩነትን የሚያመጣ ነገር አልተነሳም፡፡ ይሔ ደግሞ ተገቢ አስተያየት ነው፡፡ እኛም አስተያየቱ ተገቢ ነው ብለን ወስደነዋል፡፡
አል ዐይን፦ ተደጋግመው ከሚነሱ የዘርፉ ችግሮች አንዱ የአቅም ችግር ነው፡፡ እንዲያውም አሁን አሁን ሁኔታው ባስ ብሎ በጥሩ መልኩ መጡ የሚባሉ ሚዲያዎች ጭምር እስከመዘጋት ሲደርሱ እየተመለከትን ነው፡፡ ፖሊሲው እንዲህ ዓይነት ችግሮችን ምን ያህል ሊቀርፍ ይችላል?
ጌታቸው ድንቁ (ዶ/ር)፦ ፖሊሲው ነጻ፣ገለልተኛ እና አቅማቸው የጎለበተ ሚዲያዎች እንዲኖሩ ይፈልጋል፡፡ አቅማቸው ሲባል የኢኮኖሚ አቅማቸውም ጭምር ነው፡፡ በጥናቱ የተለየው አንዱ ችግር የሚዲያ ኢኩይፕመንት/ቁሳቁስ ላይ የተጣለው ከፍተኛ ታክስ፣ የህትመት ዋጋ ከፍተኛ መሆንም ነው፡፡ የሳታላይት ኪራይንም ይጨምራል፡፡ ኪራዩ ዝቅ እንዲል መንግስትም አግዞት በብር የሚከፍሉበትን አማራጮች መፈለግ ሁሉ ታይቷል፡፡ እሱን ተከትሎ የተጀመሩ ስራዎችም አሉ፡፡ እና እርግጠኛ ነኝ የኢኮኖሚ አቅማቸውን የሚደግፉ ነገሮች ይደረጋሉ፡፡
ሁለተኛው የሙያዊነት አቅም ነው፡፡ እዚያም አካባቢ የሚዲያውን አቅም መገንባት ያስፈልጋል፡፡ ጋዜጠኞች ፣ ሌሎች የሚዲያ ባለሙያዎች በሀገር ዉስጥና በዉጭ ሀገር ተገቢ የሆነ ስልጠና እንዲያገኙ መንግስት ይሔን ትኩረት አድርጎ እንደሚሰራበት አምኖበታል፡፡ ፖሊሲው ዉስጥም ተጠቁሟል፡፡ በሚቀጥለው አንድ ሁለት ዓመት ዉስጥ የሚታይ ነገር ይመጣል ብለን እናስባለን፡፡
አል ዐይን፦ የገለልተኛነት ችግሮች እንዳሉ ይነሳል፡፡ ሆኖም እንዲህ ዓይነት ችግሮች በፖሊሲ ብቻ ሊመለሱ አይችሉም፡፡ የባለቤትነትም ጉዳይ አለ፡፡ ‘ማን በማን ሚዲያ ላይ ይናገራል’ም ነው የሚባለው፡፡ እንዲህ ዓይነቱን እና ከባለቤትነት ጋር የተያያዘውን ችግር ፖሊሲው እንዴት ነው የሚፈታው?
ጌታቸው ድንቁ (ዶ/ር) ፦ በሙያዊነት ነው የበለጠ የሚታገዘው፣ በተወሰነ ደረጃ በኢኮኖሚ አቅም ራሱን የቻለ መሆኑም ይጠቅመዋል፡፡ ለምን ከበስተጀርባው ገንዘብን እያሳዩ ፍላታቸውን ለማራመድ የሚመጡትን ‘አይሆንም’ ይላል፡፡ የፋይናንስ ግልጽነትም ጉዳይ እዚህ ጋር ተያይዞ ሊመጣ ይችላል፡፡ የእነዚህ ሁሉ ድምር ውጤት ነው እንጂ ይሄንን ገለልተኝነትን የሚያመጣው ሙሉ በሙሉ ይጠፋል ተብሎ አይታሰብም፤ ግን በእጅጉ ሊቀነስ ይችላል፡፡
አሁን የሙያዊነቱም ችግር አለ፤ የገንዘብ ዐቅም ችግሩም አለ፡፡ ሁለቱም ተዳምረው በጣም በገዘፈ ደረጃ ጭልጥ ያለ ወገንተኝነት እየታየ ነው፡፡ የፕሮፌሽናል መገናኛ ብዙሃን ሥራን የማይመስል ነገር እየታየ ነው፡፡ ይሄ በሂደት የሚስተካከል ነው፡፡ የጋዜጠኝነቱ ባህል ሲጎለብትና ሥር ሲሰድም ጭምር የሚመጣ እንጂ በአንድ ሌሊት የሚጠፋ ችግር እንደሆነ አድርገን አናስብም፡፡
አል ዐይን፦ ከፓርቲ ጋር የተቆራኙ ‘ፓርቲ አፊሌትድ’ ሊባሉ የሚችሉ ሚዲያዎች አሉ በሚልም ይነገራል፡፡ እንዲህ ዓይነቱስ ነገር?
ጌታቸው ድንቁ (ዶ/ር)፦ ፖሊሲው ለፖለቲካ ፓርቲዎች የኤሌክትሮኒክስ ሚዲያዎችን አይፈቅም፡፡ ስለዚህ ኤሌክትሮኒክስ ሚዲያዎች ‘አፊሌሽን’ አልከው አንተ የሚስሉ ነገሮች አሉ፡፡ ከፓርቲዎች ጋር ‘አፊሌትድ’ መሆን የለባቸውም፡፡ ከሆኑ ሕግን ጥሰዋል ማለት ነው፡፡ ነገር ግን የፓርቲ ልሳን መሆኑን በትክክል ገልጸው ሲያበቁ የሕትመት ሚዲያዎችን ማራመድ ይችላሉ፡፡
ከዛ በስተጀርባ ግን የኤሌክትሮኒክስ ሚዲያዎች ጭምር ከፓርቲዎች ጋር የቀረበ ወይም የተወሰነ ቁርኝት እንዳላቸው ይሰማል እና ይሄ ተገቢ አይደለም፡፡
አል ዐይን፦ የባለቤትነት ጉዳይ እንደተጠበቀ ሆኖ ሚዲያዎች ጭራሽ በኦንላይን በሚሰበሰብ የገንዘብ ድጋፍ (ጎፈንድ ሚ) የሚደጎሙ እየሆኑ መጥተዋል፡፡ ከዛ ባሻገር የህዝብን አንድነት የሚያናጉ ስራዎችን ይሰራሉ በሚል የሚወቀሱ አንዳንድ ሚዲዎች እንዳሉም ይታወቃል፡፡ እንዲህ ዓይነቱንስ ጉዳይ እንዴት እየተመለከታችሁት ነው? ፖሊሲውስ ምን ዓይነት ምላሽ አለው?
ጌታቸው ድንቁ (ዶ/ር)፦ ልክ ነው፡፡ ይሄ ይቀጥላል ወይ አይመስለኝም፡፡ ቅድም ያልኩት የፋይናንስ ግልጽነት ጉዳይ ሚዲያዎች፤ተጠያቂነታቸው ለህዝብም ጭምር ነው፡፡ የሙያዊነት ማነስና የኢኮኖሚ ችግር ተቀላቅለው እስከዛሬ ድረስ እንዲሄድ አድርገውታል፡፡ ይሄ ግን እንዲቀጥል መፈቀድ የለበትም ነው፡፡ በሃገር ውስጥ አስቻይ ነገሮች ከተደረጉ በኋላ ከውጭ አገር የሚመጡ ያልተገቡ ሪሶርሶች/ሃብቶች ሚዲያዎችን በተለይ ደግሞ ህጋዊ ፍቃድ አውጥተው የሚሰሩ ሚዲያዎችን በዛ መልኩ ሊደገፉ አይችሉም ከዚህ በኋላ፡፡ ተጠያቂ እናደርጋቸዋለን፡፡ የገንዘብ ምንጫቸው ታውቆ በተገቢው መንገድ ኦዲት መደረግ እነሱም ግልጽ ማድረግ አለባቸው፡፡
አል ዐይን፦ ከዋናው ሚዲያ ባልተናነሰ ችግሮችን በመፍጠር ላይ ነው የሚባልለትን ማህበራዊ ሚዲያን በተመለከተስ ፖሊሲው ምን አዲስ ነገር ይዟል?
ጌታቸው ድንቁ (ዶ/ር)፦ ባለስልጣኑ እስካሁን ባለው አደረጃጀት በዋናነት ቴሌቪዥንና ሬዲዮዎችን ብቻ ነበር የሚመለከተው፡፡ የህትመት ውጤቶችን እንኳን ይመዘግባል ፍቃድ ይሰጣል እንጂ የብሮድካስት ሚዲያውን በሚከታተልበት ልክ አይከታተልም፡፡ የኦንላይን ሚዲያው በተለይ ማህበራዊ ሚዲያውም ኃላፊነታችን አይደለም በሚል ከዚህ በፊት አልተገባበትም ነበር፡፡ ነገር ግን ባለፈው ዓመት የወጣ የጥላቻ እና ሃሰተኛ መረጃ ቁጥጥር አዋጅ አለ፡፡ እሱ የትኛውም የሚዲያ አማራጭ ላይ ማህራዊ ሚዲያውን ጨምሮ የሚካሄዱ ንግግሮች የጥላቻ ሃሳቦችን ማራመድ መረጃዎችን ማሰራጨት ያስጠይቃል ይላል፡፡ በዛ መሰረት የማስተማር ተደራሲውን የማሳወቅ (ሚዲያ ሊትሬሲ) ከዚያም በተጓዳኝ በህግ የመጠየቅ ስራ ይሰራል፡፡ ፖሊስውም መታየት ካለባቸው ዘርፎች እንደሆነ አድርጎ አካቶታል፡፡
አል ዐይን፦ የባለስልጣኑ ሚዲያዎችን የመቆጣጠር ዐቅም ምን ያህል ነው? ህዝብ ባለስልጣኑ የለም ወይ ብሎ እስኪጠይቅ ድረስ ለምን ለመቆጣጠር ይዘገያል?
ጌታቸው ድንቁ (ዶ/ር)፦ ‘ዘገየ’ የሚሉ አሉ፡፡ ግን ልክ መቼ ነበር የነበረው? የትኛው ጋር ነበረ ልክ? የሚለውን በትክክል ‘እዚህ ጋ ነው’ ብሎ ሊመልስ የሚችል ሰው ደግሞ ብዙም የለም፡፡ ወይስ ነጻነቱ ጭራሽኑ መሰጠት አልነበረበትም?
ለነጻነቱ እኮ የታገለው ህዝብም ጭምር ነው፡፡ ‘ሚዲያው ታፍኗል፤ ከዚህ የተሻለ ነጻነት ይገባው ነበር፤ ጋዜጠኞች ያለአግባብ ይሰደዳሉ ይታሰራሉ’ የሚለውን ድምጽ ሲያሰማ የነበረው እኮ ህዝብም ጭምር ነው፡፡ መንግስት ያን ሰምቶ ነው ማስተካከያዎችን ለማድረግ የወደደው፡፡
አሁንም ጊዜ ሰጥቷቸው እድል አግኝተው ሲያበቁ ህዝቡ ደግሞ ‘አይ ይሄማ ልክ አይደለም’ እስከሚል ድረስ መጠበቁ ደግሞ ለመንግስት ጥሩ ነበር ብዬ ነው የምለው፡፡ ከራሱ ከህዝቡ መጣ አየህ፡፡ አሁን የመንግስት የማፈን ፍላጎት ሳይሆን ጉዳት የማድረሳቸውን ነገር ተገንዝቦ ህዝብ ስጋት ውስጥ ሲገባ ደግሞ የብሮድካስት ባለስልጣንን ዘገየ ቢሉኝ ይሻለኛል ፈጥኖ እርምጃ ወሰደ ከሚሉኝ፡፡
አል ዐይን፦ እርምጃው ህዝብ የጠየቀውን ቀርፏል ወይ ህዝብን ከህዝብ የሚያጋጩ ስራዎችን ሲሰሩ ነበር በሚል እርምጃ የተወሰደባቸው ሚዲያዎች አሁንም ከውጭ ሃገራት ጭምር እያሰራጩ እየተመለከትን ነው?
ጌታቸው ድንቁ (ዶ/ር)፦ መጀመሪያውኑ ሚዲያን የፈለጉት ፖለቲካን ለማራመድ እንጂ ለፕሮፌሽን/ለሙያው አልነበረም፡፡ ብታግዳቸውም የበለጠ ከፍተውበት ያሉትን አማራጮች ሁሉ እየተጠቀሙ ሄዱ እንጂ አልታረሙም፡፡ የተወሰኑ ሊኖሩ ይችላሉ የሚታረሙ፡፡ ይሄ እንግዲህ ለሙያው ቁርጠኝነት እንደሌላቸው ለህዝቡም ብዙ ክብር እንደሌለ የሚያሳይ ነው፡፡ ምክንያቱም “ሙያው ይሄን ይፈቅዳል አይፈቅድም” እያሉ ሳይሆን የሚሰሩት በቃ የሆነው ቢሆን ይሄን ነገር በግድ ማራመድ አለብኝ በሚል ነው፡፡
አሁንም ድረስ ከሩቅም ለሚመጡ ይዘቶች ህዝብን ከዛ ለመከላከል የአጭር የመካከለኛ እና የረጅም ጊዜ ብለን ያስቀመጥናቸው እቅዶች አሉ፡፡ እነሱንም በሂደት በምናደርጋቸው ጊዜ አሁን እንደሚያደርጉት ህገወጥ ሆነው ከሩቅ ነገሮችን ማካሄድ ይቀጥላሉ ብዬ አላምንም፡፡
አል ዐይን፦ መረጃን በቶሎ እና በተፈለገው ጊዜ የማግኘቱ ነገር ለሚዲያዎች እጅግ አዳጋች ሆኗል እና ፖሊሲው ብዙዎች የዘርፉ ተቋማት ለሚያማርሩበት ለዚህ ችግር ምን ትኩረት ሰጠ?
ጌታቸው ድንቁ (ዶ/ር)፦ ፖሊሲው መረጃን ማግኘት ለመገናኛ ብዙሃን ስራ በጣም ወሳኝ እንደሆነ ይናገራል፡፡ ነገር ግን የመረጃ ነጻነት አዋጅ አሁን በስራ ላይ ያለ አለ፤ የሚያስፈጽመው የህዝብ እንባ ጠባቂ ተቋም ነው፡፡ ሆኖም በአዋጁ ውስጥ ያሉት ነገሮች ጋዜጠኝነትን ማዕከል አድርገው ነው የጋዜጠኝነትን ባህሪ በቅጡ ተረድተው ነው የወጡት ለማለት ይቸግራል፡፡ ምናልባት ያሻሽሉት ይሆናል፡፡ ትልቁ ችግር ያለው ግን ተግባራዊነቱ ላይ ነው፡፡ በኃላፊነት ላይ የምንቀመጥ ሰዎች መረጃን ለመገናኛ ብዙሃን መስጠት አንድ የኃላፊነታችን አካል አድርገን መውሰድ አለብን፡፡ ይሄ ለሚዲያው ጥሩነት ተብሎ ሳይሆን በሚዲያው በኩል መረጃው ለሚደርሳቸው ሰዎች ክብር እና መብት ሲባል የሚደረግ ነው፡፡ ይሄን ሁሉ ከግምት ውስጥ በማስገባት መስራት ግንዛቤ መፈጠርም አለበት፡፡
አል ዐይን፦ እናመሰግናለን፡፡
ጌታቸው ድንቁ (ዶ/ር)፦ አመሰግናለሁ፡፡