በሱዳን የውሀ ግድብ ተደርምሶ ከ30 በላይ ሰዎች ሞቱ
20 መንደሮችን ባጥለቀለቀው ጎርፍ 200 ሰዎች የደረሰቡት አልታወቀም
በዘንድሮው አመት የዝናብ ወቅት ከ130 በላይ ሱዳናውን በጎርፍ ምክንያት ህይወታቸው አልፏል
በምስራቃዊ ሱዳን የሚገኝ የውሀ ግድብ ተደርምሶ ከ30 በላይ ሰዎች መሞታቸው ተነገረ።
ከፖርት ሱዳን 40 ኪሎሜትር ርቀት ላይ በሚገኝው 25 ሚሊየን ኪዩቢክ ሜትር ውሀ የመያዝ አቅም ባለው አራባት ግድብ አካባቢ የጣለ ከፍተኛ ዝናብ ግድቡ እንዲደረመስ ምክንያት መሆኑን ሮይተርስ ዘግቧል፡፡
16 ወራትን ባስቆጠረ በጦርነት ውስጥ የምትገኝው ሱዳን ጦርነቱ በመሰረተ ልማቶቿ ላይ ካደረሰው ጉዳት ባለፈ በጥገና እና ማሻሻያ እጥረት የተለያዩ መሰረተ ልማቶች ከፍተኛ ጉዳት ላይ እንደሚገኙ ተነግሯል፡፡
በትላንትናው እለት በደረሰው አደጋ ሮይተርስ የሟቾች ቁጥር 30 መሆኑን ሲዘግብ ቢቢሲ 60 መሻገሩን አስነብቧል፤ በተጨማሪም 50 ሺ ሰዎች ይኖሩባቸው የነበሩ መኖሪያቤቶች በጎርፉ ጉዳት ደርሶባቸዋል፡፡
በአካባቢው ይኖሩ የነበሩ ዜጎች አካባቢውን ለቀው በከፍታ ቦታዎች ላይ ሰፍረው ይገኛሉ፡፡
በአሁኑ ወቅት በ20 መንደሮች ላይ ጉዳት አድርሷል በተባለው አደጋ ከሞቱት ሰዎች በተጨማሪ ከ150-200 የሚደርሱ ሰዎች የደረሱበት አልታወቀም ተብሏል፡፡
በአካባቢው የነፍስ አድን ስራዎች በመከናወን ላይ የሚገኝ ሲሆን የተባበሩት መንግስታት ድርጅት የአካባቢውን ባለስልጣናት ጠቅሶ ባወጣው መረጃ የአደጋው የጉዳት መጠን የታወቀው በግድቡ ምእራብ በኩል በሚገኙ አካባቢዎች ብቻ መሆኑን ገልጾ የግድቡ የምስራቅ አካባቢ በከፍተኛ ውሀ በመሸፈኑ ያደረሰውን ጉዳት ማወቅ አልተቻለም፡፡
አራባት ግድብ የፖርት ሱዳን ዋነኛ የውሀ ምንጭ ሲሆን የሀገሪቱ ዋነኛ የቀይ ባህር ወደብ የሚገኝበት እና በርካታ የእርዳታ ቁሳቁሶች የሚተላለፉበት አካባቢ እንደነበር ታውቋል፡፡
ከዚህ ባለፈም በአሁኑ ወቅት የሱዳን መንግስት አስተዳደር የመንግስት ሀላፊዎች እና ዲፕሎማቶች መገኛ ከሆነችው ፖርት ሱዳን በቅርብ ርቀት ላይ የሚገኝ ነው ተብሏል፡፡
በዚህ የተነሳም ፖርት ሱዳንን ጨምሮ በአካባቢው የሚገኙ ከተሞች በመጪዎቹ ቀናት ከፍተኛ የመጠጥ ውሀ እጥረት እንደሚያጋጥማቸው ተመላክቷል፡፡
በትላንትናው እለት መንግስት ባወጣው መረጃ በዘንድሮው የዝናብ ወቅት በመላ ሀገሪቱ 132 ሰዎች መሞታቸውን እና 118 ሺ ሰዎች ከቀያቸው መፈናቀላቸውን ነው ያስታወቀው፡፡
16 ወራትን በዘለቀው የሱዳን ጦርነት 25.5 ሚሊየን ወይም ከሀገሪቱ አጠቃላይ የህዝብ ቁጥር ግማሽ ያህሉ በከፍተኛ የምግብ እጥረት ውስጥ እንደሚገኝ የተመድ መረጃ ያሳያል፡፡