በሱዳን መንግስትና በአሜሪካ መካከል በድርድሩ ቅድመ ሁኔታ ዙርያ በሳኡዲ ሲደረግ የነበረው ምክክር ካለስምምነት ተጠናቋል
ለ16 ወራት የቆየውን የሱዳን ግጭት ለማስቆም ሁለቱን ተፋላሚዎች ለማቀራረብ የሚደረገው ድርድር በነገው እለት በጄኔቫ መካሄድ ይጀምራል፡፡
የሱዳን ሰራዊት በድርድሩ ላይ እንደሚሳተፍ ማረጋጋጫ ባይሰጠም ድርድሩ በተያዘለት ቀጠሮ እንደሚካሄድ አሜሪካ አስታውቃለች፡፡
በአሜሪካ እና ሳኡዲ አረብያ መሪነት በሲውዘርላንድ ጄኔቫ እንዲካሄድ ለቀረበው የድርድር ጥሪ የሀገሪቱ የውጭ ጉዳይ ሚንስትር መንግስት ፈቃደኛ መሆኑን አስታውቆ እንደነበር ይታወሳል፡፡
የሱዳን የውጭ ጉዳይ ሚንስቴር ባለፈው የፈረንጆቹ ወር መጨረሻ ላይ ባወጣው መግለጫ ከፈጥኖ ደራሽ ሀይሉ ጋር ለመደራደር ፈቃደኛ ነኝ ቢልም፤ ተቀናቃኝ የሆኑት ሀምዳን ዳጋሎ የሚመሩት ጦር ከተቆጣጠራቸው ስፍራዎች እንዲለቅ እና ሌሎች አካባቢዎችን ለመቆጣጠር የሚያደርገውን ውግያ እንዲያቆም ቅድመ ሁኔታ አስቀምጧል፡፡
በተጨማሪም በድርድሩ አጀንዳዎች ዙርያ ከአሜሪካ ባለስልጣናት ጋር መነጋገር እንደሚፈልግ ገልጿል፡፡
ይህን ተከትሎ በሳኡዲ አረብያ ጂዳ የሱዳን ጦር ባስቀመጣቸው ቅድመ ሁኔታዎች ላይ ምክክር ሲደረግ ቢቆይም በሳምንቱ መጨረሻ እሁድ ያለ ስምምነት ተበትኗል፡፡
በሱዳን የአሜሪካ ልዩ መልዕክተኛ ቶም ፔሪዬሎ ከሱዳን ጦር ጋር ሲደረግ የነበረው ምክክር ያለ ስምምነት መጠናቀቁን ተከትሎ የጦሩ ተወካዮች በነገው አለት በሚጀምረው ጉባኤ ላይ እንደሚሳተፉ ማረጋገጫ ባይሰጡም ጦርነቱን ለማስቆም የሚደረገው አለምአቀፋዊ ጥረት አካል የሆነው የጄኔቫው ድርድር ይካሄዳል ብለዋል፡፡
ልዩ መልዕክተኛው አክለውም በሱዳኑ ግጭት ዙርያ አፋጣኝ ተኩስ አቁም እና ድርድር የማይካሄድ ከሆነ የተራዘመው ጦርነት ሀገሪቱን ሊያፈርሳት ይችላል ነው ያሉት፡፡
በንጹሀን ላይ በሚደርስ በደል እና የሰብአዊ መብት ጥሰት በተደጋጋሚ የሚከሰሰው የፈጥኖ ደራሽ ሀይሉ መሪ ጄነራል ሃምዳን ዳጋሎ ንጹሀንን የሚጠብቅ አዲስ የጸጥታ ሀይል ማቋቋማቸውን አስታውቀዋል፡፡ በተጨማሪም ጀነራሉ በነገው ጉባኤ ላይ ልኡካቸው እንደሚካፈል አረጋግጠዋል፡፡
ሮይተርስ እንደዘገበው የፈጥኖ ደራሽ ሀይሉ በተለያዩ ስፍራዎች የሚያደርሳቸውን የተጠናከሩ ትቃቶችን ቀጥሏል፡፡ በቅርብ ቀናት ከዋና ከተማዋ ቅርብ ርቀት ላይ በምትገኝው ኦምዱርማን በፈጸመው ጥቃት 40 የሚጠጉ ሰዎች ላይ ጉዳት ደርሷል፡፡
16 ወራትን ባስቆጠረው ጦርነት 10 ሚሊየን ሰዎች ከቀያቸው ሲፈናቀሉ በ10ሺዎች እንዲገደሉ ምክንያት ሆኗል፡፡
የቅርብ ጊዜ መረጃዎች እንደሚያሳዩት ሱዳን ካሏት 18 ክልሎች ውስጥ ስምንቱ በፈጥኖ ደራሽ ሀይሉ ቁጥጥር ስር ይገኛሉ፡፡
በነገው እለት ጄኔቫ የሚካሄደው ድርድር በአሜሪካ እና ሳኡዲ መሪነት የሚደረግ ሲሆን የአፍሪካ ህብረት ፣ ግብጽ እና አረብ ኢምሬትስ በታዛቢነት እንደሚታደሙ ተገልጿል፡፡