የተመድ የስደተኞች ከፍተኛ ኮሚሽነር በትግራይ የሚገኙ የኤርትራ ስደተኞችን ጎበኙ
“መንግስት የትግራይ ክልልን ሰላምና ጸጥታ በአስተማማኝ ሁኔታ” አስጠብቋል- ወ/ሮ ሙፈሪያት ካሚል
ኮሚሽነሩ በማይ ዐይኒ መጠለያ ጣቢያ የሚገኙ የኤርትራውያን ስደተኞችን ነው የጎበኙት
የተባበሩት መንግስታት ድርጅት የስደተኞች ከፍተኛ ኮሚሽነር ፊሊፖ ግራንዲ በትግራይ ክልል የሚገኙ የኤርትራ ስደተኛ መጠለያ ጣቢያዎችን ጎበኙ፡፡
ኮሚሽነሩ በማይ ዐይኒ መጠለያ ጣቢያ የሚገኙ የኤርትራውያን ስደተኞችን ነው የጎበኙት፡፡
በጉብኝቱ የሰላም ሚኒስትር ወይዘሮ ሙፈሪያት ካሚልን ጨምሮ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዴኤታ አምባሳደር ሬድዋን ሁሴን እና የስደተኞች እና ከስደት ተመላሾች ጉዳይ ኤጀንሲ ዋና ዳይሬክተር አቶ ተስፋሁን ጎበዛይ ተሳትፈዋል።
መንግስት የትግራይ ክልልን ሰላምና ጸጥታ “በአስተማማኝ ሁኔታ” ማስጠበቁን በጉብኝቱ ወቅት የገለጹት ወ/ሮ ሙፈሪያት ኢትዮጵያ ስደተኞችን በመቀበልና በማስተናገድ ረገድ ግንባር ቀደም ሃገር መሆኗን ተናግረዋል።
ስደተኞቹ ደህንነታቸው ተጠብቆ በትምህር እና በሌሎችም ማኅበራዊ ጉዳዮች እንዲሳተፉ ለማድረግ የሚያስችል ፖሊሲ ተቀርጾ ተግባዊ እንቅስቃሴዎች በመደረግ ላይ መሆኑንም ነው የተናገሩት፡፡
አምባሳደር ሬድዋን በበኩላቸው “ጉብኝቱ የትግራይ አካባቢን ደህንነት በተመለከተ የሚወጡ የተሳሳቱ መረጃዎችን ሐሰተኛነት ያረጋገጠ ነው” ብለዋል።
ሰላምን በማስጠበቅ ረገድ የተከናወነው ተግባር “ለአካባቢው አሁናዊ የሰላምና የደህንነት ሁኔታ ማረጋገጫ የሰጠ ነው” ሲሉም ነው የተናገሩት።
እንደ ኢዜአ ዘገባ ከሆነ ከፍተኛ ኮሚሽነር ፊሊፖ መጠለያ ጣቢያው የሚገኙ ስደተኞችን ሁኔታ ተዘዋውረው ተመልክተዋል።
ኢትዮጵያ ከ1 ሚሊዮን የሚልቁ የተለያዩ ሃገራት ስደተኞችን ተቀብላ በማስተናገድ ላይ ትገኛለች፡፡ ከእነዚህ ውስጥ መቶ ሺ ገደማዎቹ ኤርትራውያን ናቸው።
ከ 1 መቶ ሺ ስደተኞች መካከል 46 ሺ ያህሉ ትግራይ ክልል ውስጥ በሚገኙ ማይ ዐይኒ እና አዲ ሃሩሽን መሰል 4 መጠለያ ጣቢያዎች ውስጥ ነው የሚኖሩት።