ኢትዮጵያ ከካምፕ ውጭ የሚደረግ የኤርትራውያን ስደተኞች እንቅስቃሴ እንዲቆም ጠየቀች
ሆኖም ይህ የስደተኞቹን ደህንነት ለመጠበቅም ሆነ ሰብዓዊ ድጋፎችን በተቀናጀ መልኩ ለማድረስ እንዳላስቻለ ነው ያስታወቀው
መንግስት የስደተኞቹን እንቅስቃሴ በተመለከተ ባወጣው መግለጫ በርካታ ኤርትራውያን ስደተኞች አዲ አበባ ገብተዋል ብሏል
በርካታ ኤርትራውያን ስደተኞች ከመጠለያ ካምፖች እየወጡ እንደሆነ መንግስት አስታወቀ፡፡
ስደተኞቹ ከመኖሪያቸው የሚወጡት የህግ ማስከበር ዘመቻውን በወጉ ካለመረዳት የተነሳ ብሏል ዛሬ በአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ አፈጻጸም መርማሪ ቦርድ በኩል ባወጣው መግለጫ፡፡
የተጠናቀቀው የህግ ማስከበር ዘመቻ በካምፕ ውስጥም ሆነ ከካምፕ ውጭ በሚገኙ ኤርትራውያን ስደተኞች ላይ ቀጥተኛ ስጋትን ሊደቅን የሚችል አይደለም ያለው መግለጫው በትግራይ ክልል ከሚገኙት የማይ ዐይኔ እና የአዲ ሃሩሽ መጠለያ ካምፖች በርካታ ኤርትራውያን ስደተኞች ኢ-መደበኛ በሆነ መንገድ ወደ አዲስ አበባ መግባታቸውን አስታውቋል፡፡
እንዲህ አይነቱ አካሄድ ግን የስደተኞቹን ደህንነት እና ክብር ለማስጠበቅ ከማስቸገርም ባለፈ የተቀናጁ ድጋፎችን ለማድረግ ያስቸግራል ነው መረጃ ማጣሪያው ያለው፡፡
መንግስት ለስደተኞቹ የሚያደርገውን የህይወት አድን ድጋፍ ዳግም ለማስጀመር እና በሙሉ አቅም ለማስቀጠል እንዲሁም ለግንባር ቀደም ምላሽ ሰጪ ሰራተኞች ሰላሙ እና ደህንነቱ የተጠበቀ ምቹ የስራ ከባቢን ለመፍጠር በትጋት እየሰራ ይገኛልም ብሏል፡፡
የምግብ እርዳታዎች ወደ መጠለያ ካምፖቹ በመጓጓዝ ላይ ይገኛሉም ነው ያለው፡፡
ኤርትራውያኑ ስደተኞች የተጠለሉባቸው እና በትግራይ ክልል የሚገኙት መጠለያ ካምፖች በተረጋጋ ሁኔታዎች ውስጥ ይገኛሉ ካምፖቹ የፌዴራል መንግስቱ በተቆጣጠራቸው አካባቢዎች የሚገኙ ናቸው እንዳለው እንደ መረጃ ማጣሪያው መግለጫ፡፡
ይህ በመሆኑም ስደተኞቹ ድጋፎችን ማግኘት ወደሚችሉባቸው እና ቀድሞ ወደነበሩባቸው ካምፖች እየተመለሱ ነው፡፡
በዚያ ተቀብሎ ካኖራቸው ማህበረሰብ ጋር በህጋዊና ሰላማዊ መንገድ መኖር ይችላሉ ተብሏል፡፡
የረዥም ዓመታት የእንግዳ ተቀባይነት ታሪክ ያላት ኢትዮጵያ ኤርትራን ጨምሮ ከደቡብ ሱዳን፣ከሶማሊያ እና ከሱዳን ተሰደው የመጡ አንድ ሚሊዬን ገደማ ስደተኞችን በተለያዩ የሃገሪቱ አካባቢዎች በሚገኙ 26 መጠለያ ጣቢያዎች አስጠልላ እንደምትገኝም መግለጫው ጠቅሷል፡፡
በዋናነት በትግራይ ክልል በሚገኙ መጠለያ ጣቢያዎች የሚኖሩት ኤርትራውያኑ ስደተኞች አዲስ አበባን ጨምሮ በተለያዩ ከኢትዮጵያውያኑ ጋር ተቀላቅለው እና ሰርተው ሊኖሩ በሚችሉባቸው አካባቢዎች ላይ ይገኛሉ፡፡