አንድ ሆስፒታልም በአደጋው ፈርሶ ሀኪሞቹ እና ታማሚዎች በፍርስራሽ ውስጥ ታግተዋል
በኢንዶኔዢያ ሱላዌሲ ደሴት ዛሬ ጥር 07 ቀን 2013 ዓ.ም በተከሰተ ከፍተኛ የመሬት መንቀጥቀጥ አደጋ በትንሹ 42 ሰዎች መሞታቸውን ባለስልጣናት ገልጸዋል፡፡
ሲኤንኤየተባለ የሲንጋፕር ሚዲያ እንደዘገበው ፣ 6.2 ማግኒቱድ የተመዘገበው አደጋው ሌሎች በመቶዎች የሚቆጠሩ ሰዎችንም ለጉዳት ዳርጓል፡፡
እስካሁን በምዕራብ ሱላዌሲ በምትገኘው እና የ110,000 ሰዎች መኖሪያ በሆነችው ማሙጁ ከተማ የ34 ሰዎች አስከሬን ከህንጻዎች ፍርስራሽ ውስጥ ወጥቷል፡፡ በደቡብ ሱላዌሲ ደግሞ 8 ሰዎች መሞታቸው ተገልጿል፡፡
እንደ በርካታ ኢንዶኔዢያውያን በአንድ ስም ብቻ የሚጠራው የአደጋ ጊዜ ሰራተኛ አሪያንቶ “ምን ያክል ሰዎች እንደጠፉ አልታወቀም” ብሏል፡፡ እስካሁን በፍርስራሽ ውስጥ ታግተው የሚገኙ ሰዎች መኖራቸውንም ገልጿል፡፡
አደጋው በሺዎች የሚቆጠሩ ሰዎችን ማፈናቀሉም ነው የተገለጸው፡፡
በማሙጁ ከተማ የሚገኝ አንድ ሆስፒታልም በአደጋው የፈረሰ ሲሆን በሆስፒታሉ የሚገኙ ሀኪሞች እና ታማሚዎች በፍርስራሽ ውስጥ ታግተዋል፡፡
አንድ የከተማዋ ነዋሪ ባጠቃላይ በከተማዋ ከፍተኛ ጉዳት መድረሱን ተናግሯል፡፡ በርካታ ህንጻዎች ሲወድሙ መንገዶችም ተሰነጣጥቀዋል ነው የተባለው፡፡
በዚሁ የሱላዌሲ ደሴት ግዛት እ.ኤ.አ በ2018 ተከስቶ ከ2,000 በላይ ሰዎችን የቀጠፈውን የመሬት መንቀጥቀጥ ጨምሮ ኢንዶኔዢያ መሰል አደጋዎችን ከዚህ ቀደምም በተደጋጋሚ አስተናግዳለች፡፡