አደጋው የደረሰባት ከተማ እንደ ሂሮሺማ መውደሟን የከተማዋ ከንቲባ ገልጸዋል
በማዕከላዊ ክሮኤሽያ ዛሬ በሬክተር ስኬል 6 ነጥብ 3 ‘ማግኒቲዩድ’ የተለካ የመሬት መንቀጥቀጥ ማጋጠሙን መገናኛ ብዙኃን ዘግበዋል፡፡
በእስካሁኑ ማጣራት በዚህ አደጋ አንዲት ግለሰብ ህይወቷ ሲያልፍ አንድ አዋቂና አንድ ህጻን በአደጋው ከተጎዳ መኪና ውስጥ በህይወት መትረፋቸውን አሶሺዬትድ ፕሬስ ዘግቧል፡፡
የመሬት መንቀጥቀጡ የተከሰተው ከመዲናዋ ዛግሬብ በስተደቡብ ምስራቅ አቅጣጫ በምትገኘው የፔትሪንጃ ከተማ ሲሆን ቤቶችና ሕንጻዎችን ማውደሙም ነው የተገለጸው፡፡
የክሮኤሽያ ጠቅላይ ሚኒስትር አንድሬጅ ፕሌንኮቪች አደጋው ባጋጠመበት ስፍራ ተገኝተው ጉብኝት አድርገዋል፡፡ በጉብኝታቸውም አንዲት ግለሰብ በዚህ አደጋ መሞቷ መረጋገጡን አስታውቀው ከዚህ በላይ የተጣራ መረጃ እንደሌለ ተናግረዋል፡፡ ህጻናት መሞታቸውን ደግሞ የከተማዋ ከንቲባ ገልጸዋል፡፡ የፔትሪንጃ ከተማ መሃል አካባቢዎች መውደማቸውም ነው የተገለጸው፡፡
የአውሮፓ ሜዲትራኒያን የመሬት መንቀጥቀጥ ጥናት ማዕከል ፣ በሬክተር ስኬል 6 ነጥብ 3 ‘ማግኒቲዩድ’ የተለካው አደጋው ከመዲናዋ ዛግሬብ በደቡብ ምስራቅ 46 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ በምትገኘው ፔትሪንጃ ከፍተኛ ጉዳትና ማድረሱን አስታውቋ ፡፡
ዛሬ ያጋጠመው የመሬት መንቀጥቀጥ በትናንትናው ዕለትም በተመሳሳይ ቦታ ማጋጠሙ የተገለጸ ሲሆን የትናንትናው በሬክተር ስኬል 5 ነጥብ 2 ‘ማግኒቲዩድ’ የተለካ ነበርም ተብሏል፡፡
አደጋው የተከሰተባት የፔትሪንጃ ከተማ ከንቲባ ዳሪንኮ ዱምቦቪች የሞቱ ሕጻናት መኖራቸውን እና ከተማዋ መውደሟን ተናግረዋል፡፡ የመሬት መንቀጥቀጡ ፔትሪንጃ ከተማን በሁለተኛው የዓለም ጦርነት ማብቂያ አካባቢ በፈረንጆቹ ነሐሴ 6 ቀን 1945 በአሜሪካ የኒዩክለር ቦምቦች እንደወደመችው የሂሮሺማ ከተማ አድርጓታል ሲሉ ከንቲባው ተናግረዋል፡፡