እስራኤል በጋዛ በፈጸመችው የአየር ጥቃት ቢያንስ 42 ሰዎች መገደላቸው ተገለጸ
የእስራኤል ጦር ባወጣው መግለጫ "ከጥቂት ደቂቃዎች በፊት የእስራኤል ጦር ጀቶች በጋዛ የሚገኙ ሁለት የሀማስ መሰረተልማቶችን መትተዋል" ብሏል
ሀማስ ባወጣው መግለጫ "ወራሪዎች እና ናዚ መሪዎቻቸው ዋጋ ይከፍላሉ" ሲሉ ዝቷል
እስራኤል በጋዛ በፈጸመችው የአየር ጥቃት ቢያንስ 42 ሰዎች መገደላቸው ተገለጸ።
እስራኤል በዛሬው እለት በጋዛ በፈጸመችው የአየር ጥቃት ቢያንስ 42 ሰዎች መገደላቸውን ሮይርስ በሀማስ የሚመራውን የመንግስት ሚዲያ ጠቅሶ ዘግቧል።
እስራኤል በጋዛ ሰርጥ ከሚገኙት ታሪካዊ የመጠላያ ጣቢዎች ውስጥ አንዱ በሆነው በአል ሻቲ በሚገኙ ቤቶች ላይ በፈጸመችው የአየር ጥቃት 24 ሰዎች ተገድለዋል። ሌሎች 18 ሰዎች ደግሞ አል ቱፋህ በተባለ የመኖሪያ መንደር ላይ በተፈጸመ የአየር ጥቃት መገደላቸውን ዘገባው ጠቅሷል።
የእስራኤል ጦር ባወጣው መግለጫ "ከጥቂት ደቂቃዎች በፊት የእስራኤል ጦር ጀቶች በጋዛ የሚገኙ ሁለት የሀማስ መሰረተልማቶችን መትተዋል" ብሏል።
መግለጫው ተጨመሪ ዝርዝሮችን እንደሚያወጣም ጠቅሷል።
ሀማስ፣ የእስራእል የሀማስን መሰረተልማቶች መትቻለሁ የሚለውን መግለጫ በተመለከተ ያለው ነገር የለም። ሀማስ ባወጣው መግለጫ ጥቃቶቹ በንጹሀን ላይ ያነጣጠሩ መሆናቸዉን እና "ወራሪዎች እና ናዚ መሪዎቻቸው ዋጋ ይከፍላሉ" ሲሉ ዝቷል።
እስራእል በጋዛ መጠነ ሰፊ የእግረኛ እና የአየር ጥቃት እያካሄደች ያለችው፣ የፍልስጤሙ ታጣቂ ሀማስ ባለፈው ጥቅምት ወር የእስራኤልን ድንበር በመጣስ በ50 አመታት ውስጥ ከባድ የተባለ ጥቃት ማድረሱን ተከትሎ ነው።
ሀማስ በወቅቱ በፈጸመው ጥቃት 250 ሰዎችን ማገቱ እና 1200 የሚሆኑትን ደግሞ መግደሉን እስራኤል አስታውቃለች።
እስራኤል እያካሄደችው ባለው ጥቃት አብዛኞቹ የጋዛ መኖሪያ መንደሮች ወደ ፍርስራሽነት የተቀየሩ ሲሆን ከ37 ሺ በላይ ፍልስጤማውያን መገደላቸውን የጋዛ ባለስልጣናት ተናግረዋል።
የእስራኤል-ሀማስ ጦርነት አሁን ላይ ስምንት ወራትን ያስቆጠረ ሲሆን እስራኤል በሁለት የመጨረሻ ቦታዎች ላይ ማለትም በራፋ እና በደቡብ ጫፍ ዴየር አል ባላህ አካባቢ ላይ አተኩራለች።
እስራኤል ራፋን ለማጥቃት የወሰነችው የሀማስ የመጨረሻ ምሽግ በዚያ እንደማገኝ በመጥቀስ ነው።እስራኤል ራፋን እንዳታጠቃ ጫና ቢደረግባትም፣ እስራኤል አልተቀበለችውም።
በኳታር፣ ግብጽ እና አሜሪካ አማካኝነት እየተካሄደ ያለው የተኩስ አቁም ድርድርም እስካሁን ውጤት አላመጣም።
አሁን እስራኤል ከሌለባኖሱ ሄዝቦላ ጋር ያላት ፍጥጫም ወደ አጠቃላይ ጦርነት እንዳያመራ ተሰግቷል። የተመድ ዋና ጸኃፊ አንቶኒዮ ጉተሬዝ ሌባኖስ ሌላኛዋ ጋዛ እንዳትሆን እና ቀጣናዊ ጦርነት እንዳይቀሰቀስ አስጠንቅቀዋል።