እስራኤል በሊባኖስ ድንበር በኩል እግረኛ ጦሯን ለማሰማራት ዝግጅት እያደረገች መሆኗን ገለጸች
ባለፉት 8 ወራት እስራኤል እና ሂዝቦላ በሚሳይል ተኩስ ሲለዋወጡ ሰንብተዋል
ባለፉት 8 ወራት እስራኤል እና ሂዝቦላ በሚሳይል ተኩስ ሲለዋወጡ ሰንብተዋል
እስራኤል በሊባኖስ እግረኛ ጦሯን ለማሰማራት ዝግጅቷን ማጠናቀቋን አስታውቃለች፡፡
የእስራኤል የውጭ ጉዳይ ሚንስትር እስራኤል ካትዝ “እየበረታ ለመጣው የሂዝቦላ ትንኮሳ ምላሽ ለመስጠት ሁሉን አቀፍ ጦርነት ለማድረግ ዝግጅቶች ተደርገዋል” ነው ብለዋል፡፡
አሜሪካ የጋዛው ጦርነት ወደ ቀጠናዊ ግጭት እንዳያድግ ለመከላከል ወደ እስራኤል እና ሊባኖስ ልዑክ ልካለች፣ ሆኖም ከሰሞኑ እስራኤል የቡድኑን ከፍተኛ ወታደራዊ አዛዥ በአየር ጥቃት መግደሏን ተከትሎ የሁለቱ ወገኖች ግጭት እየተካረረ መጥቷል ፡፡
ባሳለፍነው ሳምንት በመጠኑ ከፍተኛ የተባለውን የሚሳኤል እና የድሮን ጥቃት ያደረሰው ሂዝቦላ የእስራኤል ሶስተኛዋ ትልቅ ከተማ በሆነችው ሃይፋ ከተማ ላይ ጥቃት እንደሚሰነዝር ዝቷል፡፡
የሂዝቦላ መሪ ሳይድ ሀሰን ነስረላህ በጃፓን እና ህንድ ኩባንያዎች የሚተዳደረውን የሃይፋ ወደብ እናጠቃለን ነው ያለው፡፡
በኢራን እንደሚደገፍ የሚነገረው ሂዝቦላ ከሊባኖስ ድንበር 27 ኪሎሜትር ርቀት ላይ የምትገኝው ሃይፋ ከተማ ኤርፖርቶች እና ወደቦችን የሚያሳይ 9 ደቂቃ ከ31 ሰከንድ የሚፈጅ የቅኝት ቪድዮ እንዲሰራጭ አድርጓል።
ይህን ተከትሎም የእስራኤል የውጭ ጉዳይ ሚንስትር እስራኤል ካትዝ በሰጡት ምላሽ “ሂዝቦላ በዚህ ጠብ አጫሪነቱ የሚቀጥል ከሆነ የጨዋታውን ህግ ልንቀይረው እንችላለን፣ እስራኤል በሊባኖስ እና በሂዝቦላ ላይ ሁሉን አቀፍ ጦርነት ለማወጅ ጥቂት ትእግስት ነው የቀራት” ብለዋል፡፡
የእስራኤል መከላከያ ጦር በበኩሉ በሊባኖስ ሁሉን አቀፍ ጥቃት ለመክፈት ወታደራዊ የዘመቻ ስትራቴጂዎችን ጨምሮ አጠቃላይ ዝግጅቶች መጠናቀቃቸውን አስታውቋል፡፡ ሂዝቦላ ደግሞ እስራኤል በጋዛ የምታደርገውን ጦርነት እስካላቆመች ድረስ በጥቃቱ እንደሚቀጥል አቋሙን ይፋ አድርጓል፡፡
በሊባኖስ እና በእስራኤል የአሜሪካን ዲፕሎማሲያዊ ልኡክ የሚመሩት አሞስ ሆችስቴይን ፕሬዝዳንት ጆባይደን ቀጠናዊ ግጭት እንዳይከሰት እንቅስቃሴ መጀመራቸውን ተናግረው ከሊባኖስ እና እስራኤል መሪዎች ጋር በጉዳዩ ላይ በዝርዝር መነጋገራቸውን ተናግረዋል፡፡
ከአሜሪካ በተጨማሪ ፈረንሳይም በዲፕሎማሲያዊ እንቅስቀሴው ላይ እየተሳተፈች መሆኑን የገለጹት ዲፕሎማቱ በትላንትናው እለት ከሊባኖስ መከላከያ አዛዦች ፣ ከምክርቤቱ አፈጉባኤ እና ከሌሎች የመንግስት ሀላፊዎች ጋር እንደተወያዩ አስታውቀዋል፡፡
እስራኤል በጋዛ ከሃማስ ጋር የምተገኝበት ውግያ መቋጫ ባለገኝበት ሁኔታ በሰሜን የሀገሪቱ ድንበር ከሂዝቦላ ጋር ሁሉን አቀፍ ውግያ የምትገባ ከሆነ የጋዝው ጦርነት ወደቀጠናዊ ግጭት እንዳያድግ ሲሰጋ የነበረው እውን እንዳይሆን ተሰግቷል፡፡