ሄዝቦላህ በትናንትናው እለት ብቻ 250 የሚጠጉ ሮኬቶችን ወደ እስራኤል መተኮሱ ተነገረ
የሊባኖሱ ቡድን በእስራኤል የአየር ጥቃት ለተገደለው ከፍተኛ አዛዡ ጠንካራ የአጻፋ እርምጃ መውሰዱን ነው ያስታወቀው
የእስራኤል የጦር አውሮፕላኖች በደቡባዊ ሊባኖስ የሄዝቦላህ የሮኬት ማስወንጨፊያ ጣቢያዎችን መደብደባቸው ተገልጿል
ሄዝቦላህ በትናንትናው እለት ብቻ 250 የሚጠጉ ሮኬቶችን ወደ እስራኤል መተኮሱ ተነገረ።
የሊባኖሱ ቡድን ከእስራኤል ጋር የተኩስ ልውውጥ ከጀመረ ወዲህ በአንድ ቀን ውስጥ ከፍተኛውን የሮኬት ጥቃት ማድረሱን ምንጮቹን ጠቅሶ ሬውተርስ ዘግቧል።
እስራኤል ከትናንት በስቲያ በደቡባዊ ሊባኖስ ጁያ በተባለ መንደር ውስጥ ስብሰባ ላይ የነበሩ የቡድኑን ከፍተኛ አዛዥ ታሌብ አብደላህ (አቡ ታሌብ) እና ሶስት ተዋጊዎች መግደሏ ይታወሳል።
ሄዝቦላህ ለከፍተኛ መሪው ግድያ በወሰደው የበቀል እርምጃም በስምንት ወራት ውስጥ ከፍተኛ መጠን ያለውን ሮኬት አስወንጭፏል ነው የተባለው።
ቡድኑ በእስራኤል ወታደራዊ ጣቢያዎች ላይ ያነጣጠሩ 17 ጥቃቶችን ማድረሱን አስታውቋል።
ኢን ዘቲን፣ አሚድ እና ሜሮን በተባሉ ከተሞች የሚገኙ ወታደራዊ እና የቅኝት ጣቢያዎች ላይ የሚሳኤል ጥቃት ማድረሱንም ነው የገለጸው።
በእስራኤል የአየር ጥቃት የተገደሉት ታሌብ አብደላህ ቀብር ስነስርአት ሲፈጸምም የቡድኑ አመራር ሃሸም ሰይፈዲን በእስራኤል ላይ የሚወሰደው የአጻፋ እርምጃ እንደሚጠናከር ዝተዋል።
የእስራኤል ጦር በበኩሉ ሄዝቦላህ በትናንትናው እለት በርካታ ሮኬቶችን ቢተኩስም ተመተው መውደቃቸውንና የተወሰኑት የእሳት ቃጠሎ ማስከተላቸውን ገልጿል።
ቡድኑ በእስራኤል ወደተያዘው የጎላን ኮረብታ 50 የሚጠጉ ሮኬቶችን ማስወንጨፉንና ከ90 በላይ ሮኬቶች ከሊባኖስ ወደ ደቡባዊ እስራኤል መተኮሳቸውንም አረጋግጧል።
በስምንት ወራት ውስጥ ሄዝቦላህ በአንድ ቀን በርካታ ሮኬቶችን ባስወነጨፈበት እለት የደረሰው ጉዳት ግን በዝርዝር አልተጠቀሰም።
የእስራኤል ጦር ለሄዝቦላህ የሮኬት ጥቃት በሰጠው ምላሽ በጄቶች የቡድኑን ሁለት የሮኬት ማስወንጨፊያ ጣቢያዎችና ሌሎች ይዞታዎች መደብደቡ ተገልጿል።
የጋዛው ጦርነት መቀስቀስ የእስራኤልና ሊባኖስን ድንበር ከፈረንጆቹ 2006 ወዲህ ከባድ ውጥረት ውስጥ ከቶታል።
ለፍልስጤሙ ቡድን ሃማስ አጋርነቱን ያሳየው ሄዝቦላህ በፈጸማቸው ጥቃቶች 18 የእስራኤል ወታደሮችና 10 ንጹሃን ተገድለው በድንበር ከተሞች የሚገኙ በመቶ ሺዎች የሚቆጠሩ እስራኤላውያን ተፈናቅለዋል።
እስራኤል በወሰደቻቸው የአጻፋ እርምጃዎችም ከ320 በላይ የሄዝቦላህ ተዋጊዎች መገደላቸውንና የቡድኑ ወታደራዊ ጣቢያዎች መውደማቸውን ትገልጻለች።
ቴል አቪቭ ሄዝቦላህ ጥቃቱን ካላቆመ እግረኛ ጦሬን አስገባለሁ በማለት ብትዝትም ተጨማሪ የጦር ግንባር ከመፍጠር ይልቅ የአየር ጥቃቱን ማጠናከርን ሳትመርጥ አልቀረችም።