የሩሲያ ጦር በዩክሬን ትምህርት ቤት ላይ ባደረሰው ጥቃት 60 ሰዎች ሳይሞቱ እንዳልቀረ እየተገለጸ ነው
የቦምብ ጥቃቱን ተከትሎ አስካሁን የሁለት ሰዎች አስክሬን መገኘቱም ተገልጿል
የሩስያ ጦር በሲቪሎች ላይ ያነጣጠረ ጥቃት እየሰነዘረ መሆኑ በተደጋጋሚ ክስ ቢቀርብበትም በሩሲያ በኩል ተቀባይነት አላገኘም
የሩሲያ ኃይሎች በምስራቃዊ ዩክሬን ሉሃንስክ በሚገኝ መንደር ትምህርት ቤት ላይ ባደረሱት የቦምብ ጥቃት 60 ሳይሞቱ እንዳልቀረ የግዛቱ አስተዳዳሪ ተናገሩ።
አስተዳዳሪው ሰርሂ ጋይዳይ እንዳሉት ከሆነ፤ ቅዳሜ ከሰአት በኋላ የሩሲያ ኃይሎች 90 የሚጠጉ ሰዎች በተጠለሉበት በቢሎሆሪቭካ በሚገኘው ትምህርት ቤት ላይ ቦምብ ጥለው ህንፃውን በእሳት አቃጥለውታል።
ጋይዳይ "እሳቱ ከአራት ሰዓታት በኋላ ጠፍቷል፣ ከዚያም ፍርስራሹ ተጠርጓል፣ እና በሚያሳዝን ሁኔታ የሁለት ሰዎች አስከሬኖች ተገኝተዋል" ሲሉ በቴሌግራም መጻፋቸው ሮይተርስ ዘግቧል።
"ከፍርስራሹ ውስጥ 30 ሰዎች እንዲወጡ የተደረገ ሲሆን፤ ከነሱ ውስጥ ሰባቱ ቆስለዋል፤ ሌሎች 60 ሰዎች በህንፃ ፍርስራሽ ስር ሳይሞቱ አልቀረም"ሲሉም አክሏል አስተዳዳሪው፡፡
ይሁን እንጂ ሪፖርቱን ወዲያውኑ ማረጋገጥ አልቻለም ተብሏል፡፡
ዩክሬን እና ምዕራባውያን አጋሮቿ በጦርነቱ ወቅት የሩስያ ጦር በሲቪሎች ላይ ያነጣጠረ ጥቃት እየሰነዘረ መሆኑ በተደጋጋሚ ክስ ቢያቀርቡም ፤ በሞስኮ በኩል ተቀባይነት አላገኘም፡፡
በማሪዮፖል ከተማ በሩሲያ ጦር በተከበበው የአዞቭስታል ብረት ፍብሪካ ውስጥ ተሸሽገው የነበሩ አዛውንቶች፣ ሴቶችና ህጻናት ፍብሪካውን ለቀው መውጣታቸውን ሩሲያና ዩክሬን ከቀናትት በፊት ማስታወቃቸው ይታወሳል።
እነዚህን ሰዎች ከፋብሪካው በሰላም የወጡት ከሳምት በፊት የተባበሩት መንግስታት ድርጅት እና ዓለምአቀፉ የቀይ መስቀል ማህበር በጥምረት ባከናወኑት ተልዕኮ መሆኑም ይታወቃል፡፡
የዩክሬኑ ፕሬዝዳንት ቮሎድሚር ዜሌንስኪ ከፋብሪካው 300 ሲቪል ሰዎች ከፋብሪካው በሰላም መውጣታቸውን ገልጸው እንደነበርም እንዲሁ የሚታወስ ነው፡፡