አምነስቲ ኢንተርናሽናል ሩሲያ ለፈጸመቻቸው "የጦር ወንጀሎች" ተጠያቂ መሆን አለባት አለ
ሩሲያ፤ በቡቻ ወንጀል ተፈጽሟል በሚል የተሰራጨው መራጃም የተጭበረበረና “ቀስቃሽ” ነው ማለቷ አይዘነጋም
የሩስያ ጦር ከቡቻ ካፈገፈገ በኋላ አስክሬኖች በጎዳናዎች ላይ እና በጅምላ ተቀብረው መገኘታቸው መረጃዎች ይጠቁማሉ
አምነስቲ ኢንተርናሽናል የሩሲያ ኃይሎች በዩክሬን መዲና ኪቭ ዙሪያ በሚገኙ ማህበረሰቦች ላይ የዘፈቀደ ግድያ መፈጸማቸው፣ የመኖሪያ ቤቶችን በቦምብ ማቃጠላቸውን እና ሲቪሎችን ማሰቃየታቸውን የሚያመለክቱ የተረጋገጡ ማስረጃዎች መሰነዱን አስታወቀ፡፡
የአምነስቲ ዋና ጸሃፊ አግነስ ካላማርድ "በሩሲያ ሃይሎች የተፈፀሙት ወንጀሎች የያዘው ሰነድ ህገ-ወጥ ጥቃቶችን እና በሰላማዊ ሰዎች ላይ ሆን ተብሎ የሚፈጸሙ ግድያዎችን ያጠቃለለ ነው" ብለዋል ።
"የእዝ ሰንሰለትን ጨምሮ ሁሉም ተጠያቂዎች ለፍርድ መቅረብ አለባቸው" ሲሉም አክለዋል ዋና ጸሃፊው አግነስ ካላማርድ፡፡
ሩሲያ የአምነስቲ ኢንተርናሽናልን እና የሂውማን ራይትስ ዎች ቢሮ ዘጋች
ድርጅቱ ቡቻን ጨምሮ በኪቭ አቅራቢያ በሚገኙ ስምንት ከተሞች ማስረጃዎችን እና የምስክር ወረቀቶችን ማሰባሰቡን ገልጿል።
የሩስያ ጦር በሚያዚያ ወር ከቡቻ ካፈገፈገ በኋላ፣ አስክሬኖች በጎዳናዎች ላይ ተዘርግተው፣ ብዙዎቹ እጃቸውን ወደኋላ የፊጥኝ ታስረው እና በጅምላ ተቀብረው መገኘታቸውን አሶሼትድ ፕሬስ ዘግቧል።
የኪቭ ግዛት አስተዳዳሪ ኦሌክሳንደር ፓቭሉክ በግዛቱ ቢያንስ 1 ሺ 235 የሲቪል አስከሬኖች መገኘታቸውን ተናግረዋል።
የዩክሬንም ሆነ ዓለም አቀፉ ማህበረሰብ ድርጊቱ ቢያወግዝም፤ ሩሲያ ግን ንጹሃንን ዒላማ የማደርግበት አንዳች ምክንያት የለም በማለት ክሶችን ውድቅ አድርጋለች፡፡
በቡቻ ወንጀል ተፈጽሟል በሚል የተሰራጨው መረጃ የተጭበረበረና “ቀስቃሽ” ነውም ብላለች ፡፡
ሆኖም አምነስቲ ኢንተርናሽናል ግን በሪፖርቱ የጦር ወንጀል ለመፈጸሙ ማስረጃዎች አሉኝ እያለ ነው፡፡
ሩሲያ ከተመድ የሰብአዊ መብቶች ምክር ቤት አባልነቷን አቋረጠች
የሩሲያ ወታደሮች በቡቻ ለፈጸሙት አሰቃቂ ግፍም አንዲት ባለቤቷ በጥይት ተደብድቦ የተገደለባትን ሴት እና ልጆቿን ዋቢ አድርጎ በማሳያነት አቅርቧል፡፡ በቦሮዲያንካ ከተማ ላይ የደረሰው የቦምብ ጥቃትም በአምነስቲ ሪፖርት ተካቷል።
ጥቃቱ ቢያንስ 40 ሰዎች የተገደሉበትና ስምንት የመኖሪያ ሕንፃዎች የወደሙበትም ነበር ብሏል አምነስቲ፡፡ በጥቃቱ ሚስቱን የተገደለችበትንና መኖሪያው መውደሙን ተከትሎ ጋራዥ ውስጥ ለመኖር የተገደደን ሁለት ሰዎችንም በሰላባነት አቅርቧል፡፡
አምነስቲ በጥቃቱ የተሳተፉ የሩሲያ 104 ኛ የአየር ወለድ ክፍለ ጦር አባላትን የሚጠቁሙ ማስረጃዎችንና ሲሰለጥኑባቸው የነበሩ መጽሃፍትን በምርመራው ማግኘቱንም በሪፖርቱ አስታውቋል፡፡